Fana: At a Speed of Life!

የፆታ እኩልነት ጉዳይ በውለታ የተገኘ ሳይሆን በሰውነታችን የተገባን መብታችን ነው-ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ ለ43 ጊዜ የሚከበረውን አለም አቀፍ የሴቶችን ቀንን ምክንያት በማድረግ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸው በአውሮፓውያኑ 1975 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመቱን ለሴቶች ሲል አውጆ እንደነበረ አስታውሰዋል።

በዚህ ሳያበቃም ከዚያ ዓመት በማስከተል ያሉትን አሥር አመታት የሴቶች ዐሥርት ዓመታት (Women’s Decade) ተብለው እንዲታሰቡ መወሰኑን ጠቅሰዋል፤ እነዚህ አመታት ዛሬ ላይ ለምናነሳቸው ታዋቂ የሴቶች መብት ማስከበሪያ የዓለም አቀፍ ሥምምነቶች መፈረም፥ መሠረታዊ የሆኑ የስርዐተ ፆታ ውይይቶች በአለም አቀፍ ደረጃ መጀመር እና የሴቶች ጉዳይ መታሰቢያ በዓላት መፈጠር ምክንያት ሆነው አልፈዋል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ።

እኛ ኢትዮጵያውያንም ዛሬም አለም አቀፉን የሴቶች ቀን ዘንድሮ ለ43ኛ ጊዜ ስናከብር ባለፉት አራት አስርተ አመታት የሀገራችን ሴቶች ሕይወት ምን ያህል ተለውጧል? እኛስ የሚገባንን አድርገናልን? ብለን መጠየቅም ይገባናል ብለዋል።

ይህን ጥያቄም በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በየእለቱ ልንጠይቅ፡ አጥጋቢ ያልሆኑ ምላሾችንም ልንሞግት ይገባናል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ የፆታ እኩልነት ጉዳይ በውለታ የተገኘ ሳይሆን በሰውነታችን የተገባን መብታችን ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የመብት ጉዳይ ደግሞ በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በየእለቱ በመቆጨት እና በሀላፊነት ስሜት ልናነሳውና ልንሰራበት የሚገባ ነው ብለዋል ባስተላለፉት መልዕክት።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገራችን ውስጥ የሴቶችን ውክልና ለማረጋገጥ የሚወሰዱ ውሳኔዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ በፌደራል መንግስት ካቢኔ ውስጥ የሴቶች ድርሻ ሀምሳ በመቶ መሆኑ፡ ብቃት ያላቸው ባለሙያ ሴቶች በተለያዩ ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ መሾማቸው መልካም ጅምር እና ለወጣት ሴቶች እና ወንዶች ተምሳሌት እንደሚሆንም ጠቅሰዋል፡፡

በእርግጥም በሴቶች ጉዳይ ላይ የተመዘገቡት ውጤቶች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። ነገር ግን ይህ ጅምር “የሴቶች ጥያቄ ተመልሷል! የሚበቃቸውን አግኝተዋል!” የሚል ስሜት ሊፈጥርም ሆነ እጃችን ላይ ካለው ሥራ ሊያዘናጋን አይገባምም ነው ያሉት።

ለዚህም የስርዐተ ፆታ ልዩነትን ለማጥፋት ከሰሀራ በታች ላሉ ሀገራት አሁን ባለው አያያዝ 135 አመት እንደሚፈጅ በተለያዩ መድረኮች መጠቀሱን አንስተዋል፤ በሀገራችን ደግሞ ያላቻ ጋብቻ የሴት ልጅ እና ግርዛት ዛሬም እንደሚካሄድ በመጥቀስ።

ፕሬዚዳንቷ በመልዕክታቸው ከወንዶች ተማሪዎች በላቀ ቁጥር ሴት ልጆቻችን ከመጀመሪያ፥ ከሁለተኛ ደረጃ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ትምህርታቸውን እንደሚያቋርጡ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ሰዓት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች ውስጥ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ ሴቶች 34 በመቶ፣ የሁለተኛ ዲግሪ መርሀ ግብር 17 መቶ እንዲሁም የዶክትሬት መርሀ ግብር ውስጥ ደግሞ 8 በመቶ ብቻ መሆናቸውን በመልዕክታቸው አስፍረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ሴት ልጆች ትምህርታቸውን እየተከታተሉም የቤት ሥራ ጫናን ይሸከማሉ ለፆታዊ ጥቃትም ይጋለጣሉ። ይህን ተቋቁመው ያለፉት ደግሞ ብቃታቸውን ተማምኖ የሚቀጥር፥ ይገባታል ብሎ በስራ የሚያሳድግ እንዲሁም የእነሱን ማደግ እና መለወጥ ፈልጎ የሚሰራ ተቋም እና ማህበረሰብ ባለማግኘት እንደሚንገላቱም አውስተዋል።

ከሁሉ በላይ ደግሞ በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍል ያሉ እናቶች እና ህፃናት የድህነትን መራር ገፈት በዋናነት እየተቀበሉ እንደሚኖሩ አብራርተዋል፡፡

እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተያያዥ እና ተመጋጋቢ ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቷ የሚያስተሳስራቸው ዋነኛው ሰበዝ ለሴቶች እንደማህበረሰብ የምንሰጠውን ቦታ የሚቀርፁ በዘመናት ውስጥ የደረጁ ጎታች አስተሳሰቦች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህ ጎጂ ልማዶች እና አስተሳሰቦች የባህላችን እና እሴቶቻችን አንድ አካል ናቸው። ስለ ስርዐተ ፆታ እኩልነት ያለን አስተሳሰብ ካልተለወጠ፡ ሴቶችን እንደ ሙሉ ሰው እና አቻ ዜጋ እስካላየን ድረስ ትርጉም ያለው እና ዘላቂ ለውጥ ልናመጣ አንችልም ብለዋል።

ፕሬዚዳንቷ ወደፊት መራመድ ከፈለግን እንደ ማህበረሰብ በመጀመሪያ ደረጃ መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ እንዳለብን እና 51 በመቶ የሚሆነውን የህብረተሰባችንን ክፍል እየገፋን መሆኑን መገንዘብ ያሻል። የመፍትሄ ህሳቦቻችንም ይህንን ያገናዘቡ መሆን አለባቸው ነው ያሉት።

በአመራር ቦታዎች ላይ በዘላቂነት በቂ ሴቶች እንዲኖሩ ተቋማቶቻችን በእኩልነት እንዲመሩ ከተፈለገ ሴት ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ መደገፍ እና በመንገዳቸው ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡

በፆታ የሚደረግ መድሎ እንዲወገድ ከተፈለገም እነዚህ ተግዳሮቶች ከየት ነው የሚመጡት፥ ህብረተሰቡስ ሴቶችን በዚህ መልኩ የሚፈርጀው ለምንድነው ብለን መጠየቅ አለብን ያሉ ሲሆን እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ስንጠይቅ ችግሩን ከስር መሰረቱ የመፍታት እድል ይጨምራል ብለዋል።

ሰብዐዊነት ውስጣችን ሲገባ የሰብዐዊ መብት መረዳታችን ምሉዕ ሲሆን ማንም ወገን ሲገፋ እና ሲጠቃ አይተን ዝም ማለት አንችልም ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እንደሴቶች ደግሞ እህትማማችነት በመሀላችን ሲፀና እኩልነትን ለሁሉም እንሻለን፣ በአገኘነው አጋጣሚ ሁሉ፥ ለኛ የተከፈተውን በር ከኋላችን ለምትመጣው ክፍት አድርገን ይዘን አለሁልሽ እንላለን።

እነዚህን ለማድረግ በአመት ውስጥ 365 ቀናት እንዳሉ ይህንምም መጠቀም እንደሚያስፈልግ በመግለፅ የዛሬው አይነት በዓላትም ማስታወሻ ይሆኑናል።

ነገር ግን ከአራት አስርት አመታት በፊት የወቅቱን ሁኔታ ተገንዝበው ተጨማሪ ጊዜ አሳውጀው ብዙ ተግባራትን እንዳከናወኑት ሁሉ እኛም ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ የሴቶች ቀን በአመት አንዴ ብቻ ታስቦ በመዋል መታለፍ የለበትም።

የስርዐተ ፆታ ጉዳይን ብሄራዊ አጀንዳ አድርገን ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደን የኢትዮጵያውያን ሴቶች ወር (የሴቶች ወር) ብለን ብናከብር መልካም ይሆናል ብለዋል።

ይህ ጊዜም በሀገር ደረጃ ህብረተሰባችንን፥ ባህላዊ እሴቶቻችንን እና ታሪካችንን እየፈተሽን የሚበጁንን እያፀናን እና እያከበርን እንድንቀጥል መሻሻል ያለባቸውን እየለየን እየለወጥን እንድንሄድ ተሰባስበን የምንመክርበት ይሆናል።

እንዲሁም ለለየናቸው ችግሮች መፍትሔ የምንፈልግበት፣ ያሉንን ብርቱዎች የምናደንቅበት፣ እስካሁን ከሠራነው የምንማርበት ይሆናል። ይህን መርሀ ግብር የትኛው ወር ላይ ብናደርገው መልካም ነው የሚለውን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተን የምናሳውቅ ይሆናል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ገልፀዋል።

በመጨረሻም በዚህ ሰዓት ሀላፊነት ተሰምቷችሁ ባላቸው አቅም የሴቶችን ህይወት የተሻለ ለማድረግ፣ የሀገራችንን ተቋማት ፍትሀዊ እና አሳታፊ ለማድረግ ለሚተጉት ሁሉ ምስጋናዬ አቀርባለሁ ብለዋል።

የማህበራዊ ለውጥ ሥራ ጊዜ የሚፈጅ እና ትእግስት የሚጠይቅ መሆኑን ተገንዝበን የወደፊቱን ተስፋ ሰንቀን እርስ በርስ እየተደጋገፍን እንድንሰራ ይሁን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው በሀገራችን ዙርያ ያሉ ሴት ኢትዮጵያውያን በሙሉ ያለ ሥጋት ውለው የሚያድሩባት፣ በሴትነታቸውም በፍፁም አንሰው የማይታዩባትን ኢትዮጵያን ሴቶች እና ወንዶች በጋራ እንገንባ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የዛሬ አመት እስካሁን ከተመዘገበው የላቀ መልካም የእኩልነት እና ፍትህ ዜና የምንሰማበት፣ ብዙ ሴቶች በህዝብ ተወክለው ለምርጫ የሚወዳደሩበት እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻችን የተሻለ ቁጥር ያላቸው ሴቶች የሚመረቁበት ይሁን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

You might also like
Comments
Loading...