Fana: At a Speed of Life!

የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ የአንድ ዓመት ቆይታ በምሁራን ዕይታ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2011 (ኤፍቢሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት በያዝነው የመጋቢት ወር ላይ ነበር በሀገሪቱ ምክር ቤት ቃለመሀላ ፈጽመው ስልጣን የያዙት።

በሹመታቸው ዕለት ያደረጉት የብዙሃንን ቀልብ የያዘ ንግግር እና የገቧቸው ቃሎችም ከጅምሩ ብዙ ተስፋ እንዲጣልባቸው አድርጓል።

ብዙም ሳይቆዩ በሹመታቸው እለት የተናገሯቸውን እና ቃል የገቧቸውን ጉዳዮች ወደ ተግባር መቀየር ሲጀምሩ ደግሞ በህዝቡ ዘንድ የነበረው ተስፋ ወደ ሰፊ ድጋፍ እንዲቀየር አድርጓል።

የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ በውጭ ሀገራት ትጥቅ አንግበው ይንቀሳቀሱ የነበሩትን ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡና በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበዋል።

እንዲሁም የፖለቲካ እስረኞች መፈታት፣ የኢትዮ ኤርትራ እርቅ እና የመንግስት ተቋማትን በከፊልና በሙሉ ወደ ግል ማዞር በቀዳሚነት ከሚጠቀሱላቸው አበይት ውሳኔዎቻቸው ዋነኞቹ ናቸው

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በነዚህ ስኬቶች እና ስኬቶቹ በፈጠሩላቸው ድጋፎች ታጅበው የስልጣን ዘመናቸውን በደማቁ ቢያጋምሱም ጥያቄዎች እንዲነሳባቸው የሚያደርጉ ፈተናዎች የአንድ አመት የስልጣን ዘመናቸው መጠናቀቂያን ያደበዘዙት ይመስላል።

የፌደራሊዝም ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ኃይለየሱስ ታዬ እንደሚሉት የሰዎች መፈናቀል መበራከት፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የአቋም ግልጽነት አለመኖር እና በሚመሩት ድርጅት ውስጥ የሚስተዋሉ የሃሳብ ልዩነቶች ከስኬት አደብዛዦቹ ከሆኑት ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ይላሉ።

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚናገሩት ልክ ጉዳዮችን እንዲተገብሩ በመዋቅሩ ውስጥ ያሉ አመራሮች ተመሳሳይ አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይገባል አሁን ባለው ሁኔታ ግን ነገሮች ከዚህ የተለዩ ሊሆኑ እነደሚችሉ ነው ያደረባቸውን ስጋት የሚገልጹት።

እንዲሁም ምሁሩ ከምንም በላይ ከግጭት ይልቅ በትብብር ላይ የተመሰረ ፖለቲካ እንዲኖር መስራት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀዷቸው እና የሚናገሩት ዕቅድ እንዲሳኩ ከፈለጉ አንድ ፓርቲ በአብዛኛው የተመሳሳይ ሀሳብ እና አቋም ያላቸው ሰዎች ስብስብ እንደመሆኑ በፓርቲያቸውና በመዋቅሮቻቸው ውስጥ ያሉት አመራሮች ተመሳሳይ አመለካከቶች እንዲኖራቸው ተጽእኖ መፍጠር ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ግትር አቋም ከሚያራምዱ ይልቅ አስታራቂ ሀሳብን በመቻቻል ሊያመነጩ የሚችሉ ለዘብተኛ ወይንም ተራማጅ ሰዎችን በዙርያቸው እና በድርጅታቸው እንዲበራከት ማድረግ እንደሚገባቸው የፌደራሊዝም ጉዳዮች ረዳት ፕሮፌሰሩ ሃይለየሱስ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር እና በአሜሪካው የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ አጥኚ የሆኑት አቶ አባይ ይመር ደግሞ ጥናት የሚያደርጉበትን የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ግኝትን መሰረት በማድረግ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉትን እና ለመሪዎችም ፈተና ሊሆኑ የሚችሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ሁለት አይነት መልክ እንዳላቸው አንስተዋል።

ምሁሩ የመጀመሪያ መልክ ሲጠቅሱ ቴክኒካዊ ችግር መሆኑን አንስተው፥ ይህም ከአስተዳደራዊና ከከአሰራር ከበጀት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለመፍታትም እጅግ ቀላል ነው ብለዋል።

ሁለተኛው መልክ ደግሞ የባህሪ ለውጥ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህኛው ለማሳካት ከባድ መሆኑን አንስተዋል።

ከባድ የሚያደርገውም አሁን ከገጠመን ችግር በላይ የሚገጥመን ምንድነው ብሎ ማጥናት ያስፈልጋል።

ጉዳይ ላይ መሪው ባያምንበትም እንኳን ያንን ማዳመጥ እና ሀሳቦችን አስማምቶ መሄድ ስለሚኖርበት አስቸጋሪ ነው ይላሉ።

ይህንንም ለመፍታት በጋራ ኢትዮጵያዊነትን ሊያስተሳስሩ በሚችሉ የጋራ ጎዳዮች ላይ በማተኮር ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ገልጸዋል።

 

በትእግስት አብርሃም

 

 

You might also like
Comments
Loading...