Fana: At a Speed of Life!

የገቢዎች ሚኒስቴር በኦሮሚያ ክልል ለተፈናቀሉ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎችና ለህግ ታራሚዎች ከ52 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር በኦሮሚያ ክልል ለተፈናቀሉ ከ1 ነጥብ 3ሚሊየን በላይ ዜጎችና በክልሉ ማረሚያ ቤቶች ጠያቂ ለሌላቸው የህግ ታራሚዎች ከ52 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

የገቢዎች ሚንስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ለለውጡ መስዋዕት በመሆን ያለጥፋታቸው ከቀኤያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ማቋቋም ይገባል ብለዋል።

“እስከዚያው ድረስ ግን ህመማቸው ህመማችን ነውና ድጋፍ እናደርግላቸዋለን” ብለዋል ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች በርክክቡ ላይ።

በየእስር ቤቱ የሚገኙ ታራሚዎችም ባጠፉት ጥፋት ታርመው እንዲስተካከሉ እንጂ እንዲጎዱ ስለማንፈልግ በየማረሚያ ቤቱ ጠያቂ የሌላቸውን መርዳት ተገቢ ነውም ብለዋል።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አክለውም፥ ህብረተሰቡም ህገ ወጦችን በመቆጣጠሩና ኮንትሮባንድን በመከላከሉ ረገድ የጀመረውን ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ በሌሎች ክልሎችና አከባቢዎችም ይቀጥላል ብለዋል የገቢዎች ሚኒስቴር ምንስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው፥ የተቸገሩ ወገኖችን የመርዳት ስራ ሀገራዊ ሃላፊነት ነውና ህገወጦችን ወደ ህግ ከማቅረብ ጎን ለጎን የተቸገሩ ዜጎቻችን እንረዳለን ብለዋል”

የገቢዎች ሚኒስቴር ከአከባቢያቸው ለተፈናቀሉና በማረሚያ ቤቶች ጠያቂ ለሌላቸው ዜጎች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሚኒስቴሩ በተያዘዉ በጀት ዓመት ብቻ በደቡብ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች 123 ሚሊየን ብር የሚገመቱ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።

You might also like
Comments
Loading...