Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ ፈረንሳይ የቢስነዝ ፎረም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮ ፈረንሳይ የቢዝነስ ፎረም  በዛሬው ዕለት ተካሄደ::

 በዚህ የቢዝነስ ፎረም ላይ የተሳተፉ 26 የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

በቢዝነስ ፎረሙ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ ለልኡካኑ በኢትዮጵያ ስለላለው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የፈረንሳይ የቢዝነስ ልኡክ መሪ ፍሊፕ ጉሬድ ከማብራሪያው በኋላ በሰጡት መግለጫ ኩባንያዎቹ በሀይል፣ በመሰረተ ልማት፣  በቴክኖሎጂ እና በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት መሰማራት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

በተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በመግባትም ኢንቨስት ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ዙሪያ መምከራቸውን ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል ለማዘዋወር መወሰኗ እና ሌሎች መልካም አጋጣሚዎችም ኩባንያዎቹ በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎታቸውን እንዳሳደገ መግለፃቸው ተጠቁሟል፡፡

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ያደረጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ተከትሎ ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎቸ  በጋራ ለመስራት መስማማታቸው የሚታወስ ነው።

እነዚህ ስምምነቶች ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በህዋ ሳይንስ እና በኢኮኖሚው ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል።

ስምምነት ከተደረሳባቸው ሰባት ዘርፎች መካከል ስድስቱ  ከግል ኩባንያዎች ጋር ሲሆን፥ አንዱ በመንግስት ደረጃ የተደረሰ  መሆኑም ተጠቁሟል።

ስምምነቶቹም፡-

  1. የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከፈረንሳዩ ብሄራዊ የህዋ ምርምራ ማዕከል ጋር በህዋ ሳይንስ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
  2. የኢትዮጵያ ኢንቨስትመነት ኮሚሽን ከካስቴል ግሩፕ ጋር የበቆሎ ማቀነባበሪያ ለመገንባት የደረሱት ስምምነት ተጠቃሽ ነው።
  3. ሌላው ስምምነት ሲኤምኤ ሲጂኤም የተባለ የፈረንሳይ የኮንቲነር ትራንስፖርት እና የመርከብ ኩባንያ ከኢትዮጵያ  ከተሰማራውና የሎጀስቲክ አገልግሎት ከሚሰጠው ኤም ኤ ሲ ሲ ኤፍ ኤ ኩባንያ ጋር በሽርክና ለመስራት የተስማሙበት ነው።
  4. የኢትዮጵያ መርከቦችና ሎጀስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ሲ ኤም ኤ ሲ ጂ ኤም ከተባለው የፈረንሳይ የኮንቲነር ትራንስፖርት እና የመርከብ ካምፓኒ ጋር የሞጆ ደረቅ ወደብን ለማስተዳደር ተስማምተዋል፡፡
  5. የኢትዮጵያ ፋይናስ ሚኒስቴር ከሜሪዳይም ግሎባል ኢንፍራስትራክቸር ሀብ ጋር የአፍሪካ የመሰረተ ልማት ትምህርት መርሃ ግብር (ኤ አይ ኤፍ ፒ) ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርዋል።
  6. በተመሳሳይ ቦሎሬ አፍሪካ ሎጀስቲክ የተሰኘ የፈረንሳይ ኩባንያ ሲ ኤል ኤስ ሎጀስቲክ ከተሰኘ የኢትዮጵያ ኩባንያ ጋር በሽርክና ለመስራት ተስማምተዋል።
  7. እንዲሁም አቶ ቴዎድሮስ የተባሉ ግለሰብ ካናል ፕላስ ግሩብ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር የፈረንሳዩን ፔይ ቲቪን ለማስተዋወቅ ተስማምተዋል።

በፋሲካው ታደሰና በኤፍሬም ምትኩ

You might also like
Comments
Loading...