Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች በኢትዮጵያ አየር ክልል እንዳይበሩ አገደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የቦይንግ 737 ማክስ 8 እና ማክስ 9 አውሮፕላኖች የተሰኙ አውሮፕላኖች በኢትዮጵያ አየር ክልል እንዳይበሩ አገደ።

የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አንሙት ለማ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ባለስልጣኑ ቦይንግ 737 ማክስ 8 እና ማክስ 9 አውሮፕላኖች በኢትዮጵያ አየር ክልል ወስጥ እንዳይበሩ ሙሉ በሙሉ ተከልክሏል።

እገዳውን መነሻ በማድረግም በኢትዮጵያ አየር ክልል ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግም ነው ያስታወቁት።

ባሳለፍነው እሁድ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን ላይ በደረሰ የመከስከስ አደጋ የ157 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትሎ በርካታ ሀገራት አውሮፕላኑን በማገድ ላይ ይገኛሉ።

እስካሁንም የቦይንግ 737 ማክስ 8 እና ማክስ 9 አውሮፕላኖችን ያገዱ ሀገራት ከ50 መብለጣቸውንም ነው እየወጡ ያሉ መረጃዎች የሚያመለክቱት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሳለፍነው እሁድ ያሉትን ሁሉንም ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖችን ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አገልግሎት ማስወጣቱ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም ቻይና፣ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ የአውሮፓ ህብረት፣ አውስትራሊያ እና ካናዳ አውሮፕላኑ በሀገራቸው ውስጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል እና በአየር ክልላቸው እንዳይበር ካደጉ ሀገራት ውስጥ ናቸው።

የአሜሪካ የፌደራል አቩዬሽን አስተዳደር ቦይንግ 737 ማክስ የተሰኙ አውሮፕላኖች ላልተወሰነ ጊዜ በአሜሪካ አየር መንገዶች ጥቅም ላይ እንዳይውል እና አውሮፕላኑ በአሜሪካ የአየር ክልል ውስጥ እንዳይበር በዛሬው እለት ትእዛዝ ማሳለፉም ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like
Comments
Loading...