Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በግብር ስወራና በተመሳሳይ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 1ሺህ 700 ነጋዴዎች ክስ እንዲቋረጥ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 2፣ 2011(ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በግብር ስወራ፣ በሃሰተኛ ደረሰኝ እና ደረሰኝ ስወራ የተጠረጠሩና ጉዳያቸው በክስ ላይ የሚገኙ 1 ሺህ 700 ነጋዴዎች ክስ እንዲቋረጥ ጠየቀ።

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በፃፉት ደብዳቤ በነጋዴዎቹ ላይ የተከፈተው ክስ እንዲቋረጥ ጠይቀዋል።

ምክትል ከንቲባው ከግብር ከፋዩ ጋራ በተደረገ ውይይት ትልልቅ ህገ ወጥ ግብር ከፋዮች ላይ ትኩረት አለመደረጉን እና አነስተኛ ግብር ከፋዮችን ብቻ መቆጣጠርና እርምጃ መወሰዱ አግባብነት የሌለው መሆኑ መታመኑን አመልክተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ይህን ቅሬታ መነሻ በማድረግና በማጣራት መንግስት የጀመራቸው የቀረጥና የኮንትሮባንድ ቁጥጥሮችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያመለከቱት።

የንግድ ስርዓቱ ላይ ፍትሃዊ አሰራር ለመጀመር እንዲቻል በነጋዴዎቹ ላይ የተከፈተው ክስ እንዲቋረጥላቸው መጠየቁ ተጠቅሷል።

ጉዳያቸው በምርመራና በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በክስ ላይ ያሉ ግብር ከፋዮች የክስ ይቋረጥ ጥያቄን በመመርመር በቀጣይ ምላሽ እንደሚሰጥ ተገልጿል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like
Comments
Loading...