Fana: At a Speed of Life!

ከ10 ቢሊየን ብሩ ተዘዋዋሪ ፈንድ ውስጥ ከ9 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላዩ ለክልሎች ተለቋል

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ከተመደበው 10 ቢሊየን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ውስጥ ከ9 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላዩ ለክልሎች መለቀቁን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሃገሪቱ ከወጣቶች የስራ ፈጠራ እድል አንጻር ያለውን ክፍተት ለመቅረፍ በ2009 ዓ.ም የ10 ቢሊየን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱ ይታወሳል።

የፌደራል የከተሞች ስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ለጣቢያችን እንደገለጸው፥ ከ10 ቢሊየን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ውስጥ ለከተሞች 4 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ተለቋል።

በዚህም በማምረቻ፣ ግንባታ፣ ከተማ ግብርና፣ ንግድና አገልግሎት ዘርፍ በርካታ ወጣቶችን ማሰማራት መቻሉን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ ተናግረዋል።

ባለፉት ሶስት አመታት ከ25 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት ከ146 ሺህ በላይ ወጣቶችን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ በ2010 ዓ.ም 4 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ለክልሎች መሰራጨቱን ያነሳል፤ ባለፉት ሰባት ወራትም 954 ሚሊየን ብር ለክልሎች ተለቋል ነው ያለው።

አራት ክልሎችም የተመደበላቸውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ መውሰዳቸውን የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ ይናገራሉ።

ከተዘዋዋሪ ፈንዱ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የተመደበለትን የአማራ ክልልን ጨምሮ፥ ደቡብ፣ ሀረሪ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ወስደዋልም ነው ያሉት።

የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ከ10 ቢሊየን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ውስጥ 91 ነጥብ 6 በመቶው ለክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ተለቋል፤ ይህም 9 ቢሊየን 125 ሚሊየን 756 ሺህ 385 ብር ከ25 ሳንቲም ተሰራጭቷል እንደ ማለት ነው።

ቀሪ 874 ሚሊየን ብሩ ደግሞ በዚህ አመት ይተላለፋል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ሀጂ ኢብሳ እንደነገሩን የጋምቤላ ክልል ከተመደበለት 50 ሚሊየን 35 ሚሊየን ብሩን የወሰደ ሲሆን፥ ቀሪ 15 ሚሊየን ብሩም በቅርቡ ይለቀቅለታል።

ከአራቱ ሙሉ በሙሉ ተዘዋዋሪ ፈንዱን ከተጠቀሙ ክልሎች ውጭ ያሉት ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ቀደም ሲል የወሰዱትን ገንዘብ ለምን እንዳዋሉት ሪፖርት ካቀረቡም ገንዘቡ በፍጥነት ይለቀቅላቸዋል ነው ያሉት አቶ ሀጂ።

የአፋር ክልል ከተዘዋዋሪ ፈንዱ 206 ሚሊየን ብር ተመድቦለት 83 ሚሊየን ብር አካባቢ ወስዷል፤ በዚህም ከ3 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ቢታሰብም የታቀደውን ያህል ግን ወደ ስራ አልተገባም።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፈንዱ የተመደበለትን 418 ሚሊየን ብር ሙሉ በሙሉ ወስዶ ወጣቶችን ወደ ስራ አስገብቷል።

የስራ ፈላጊው ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎም በቅርቡ 2 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት ለስራ እድል ፈጠራ መድቧል።

ሌሎች ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮችም ይህን በመከተል ተጨማሪ በጀት ሊይዙ ይገባል የሚለው ሚኒስቴሩ፥ በተዘዋዋሪ ፈንዱ የተላለፈውን ገንዘብ አስመልሶ ለአዳዲስ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ማዘዋወር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስቧል።

የፌደራል የከተሞች ስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዘነበ ኩሞም፥ ለወጣቶች አስተላልፈውት የነበረውን ገንዘብ በማስመለስ ለአዳዲስ ወጣቶች መስጠት የጀመሩ ክልሎች መኖራቸውን ያነሳሉ።

ኤጀንሲው በ2011 ዓ.ም ለ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ እድሎችን ለመፍጠር አቅዶ እየሰራ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በእስካሁኑ ሂደት ከ1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

 

 

በፋሲካው ታደሰ

You might also like
Comments
Loading...