Fana: At a Speed of Life!

ኦዲፒ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) እንደ ሀገር የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) 29ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማስመልከት በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ ነው ይህንን ያለው።

ፓርቲው በመግለጫው ባለፉት ዓመታት የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መብቶችን ለማስጠበቅ የኦሮሞ ህዝብ እና የኦሮሞ ታጋዮች የታገሉለት ዓላማ እንዲሳካ ባደረገው መራራ ትግል ታሪክ የሚያወሳው አኩሪ ስራዎችን መስራት ተችሏል።

በየጊዜው ከሚጨምረው የህዝብ ፍላጎት ጋር በተያያዘ ከህብረተሰቡ የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲም ከልማት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ህዝቡን በማዳመጥ እንዲሁም መስተካከል ያለባቸውን ችግሮች እያስተካከለ መሄዱን አስታውቋል።

ፓርቲው በየጊዜው እያጎለበተ በመጣው የዴሞክራሲ እና የህዝባዊ ወገንተኝነት ባህል መሰረትም ከህብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን በማዳመጥ፣ ከልብ ይቅርታ በመጠየቅ እና የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ወደ ስራ እየቀየረ ወደ ጥልቅ ተሃድሶ በመግባት ጉዞውን ማደሱን ገልጿል።

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ በኦሮሞ ስም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላቶቻቸው የታሰሩባቸው በሙሉ እንዲፈቱ እንዲሁም በውጭ ሀገራት ሆነው ሲታገሉ የነበሩ በሙሉ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉንም በመግለጫው አስታውሷል።

ከዚህ በተጨማሪም ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዲሁም ፍትሃዊ የፖለቲካ ተሳትፎ በማድረግ የኦሮሞን ህዝብ ፍላጎት ለማሟላት በዘራፊዎች ላይ በተወሰደው እርምጃና በክልሉ የተጀመረው የኢኮኖሚ አብዮት በህብረተሰቡ ዘንድ ተስፋ ማሳደሩን ገልጿል።

የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ችግሮችን ከመቅረፍ በዘለለም በመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዘው ያሉ ችግሮችን ከመሰረታቸው ለመፍታት እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ስራዎችም የህብረተሰቡን ፍላጎት ከማሟላት አልፎ ለክልሉ እና  የሀገሪቱን መፃኢ እድል እያረጋገጠ መሆኑንም ጠቅሷል።

እንደ ሀገርም ይሁን እንደ ክልል ሰላምንና የህግ የበላይነት መረጋገጥ አለበት ያለው ፓርቲው፥ ሆኖም ግን አንዳንድ የፖለቲካ ነጋዴዎች አሁን በሀገሪቱ የታየውን የለውጥ ተስፋ ለማደናቀፍ ቢፈልጉም ኦዲፒ እና በፓርቲው የሚመራው መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ አስተማማኝ ሰላም እየተረጋገጠ መጥቷል ብሏል።

የኦሮሞ ህዝብ እና ሁሉም ሀገሪቱ ህዝቦች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በጥናት ላይ በመመስረት እንደ ቅደም ተከተላቸው ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ የጀመራቸውን የለውጥ ስራዎች ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል።

የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በአንድነት በመሆን በሁሉም መስክ የተጀመረው ለውጥ እንዲያስቀጥል ኦዲፒ ጥሪ አቅርቧል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ለውጥ የመጣው ወጣቶች በከፈሉት መሰዋእትነት ነው ያለው ፓርቲው፥ ወጣቶች ዛሬም እንደ ትናትናው ሁሉ ትግላቸውን በሰላማዊ እና በተረጋጋ መልኩ በመቀጠል የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

ኦዲፒ ለኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ባስተላለፈው መልእክትም፥ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ደስታቸውን እና የሚያጋጥሙ ችግሮቻቸውን ወንድማቸው ከሆነው የኦሮሞ ህዝብ ጋር አብረው ታግለው አልፈዋል ብሏል።

የኦሮሞ ህዝብ እና ኦዲፒ ዛሬም እንደ ትናንቱ ወንድማማችነትና አብሮነት እንዲሁም መልካም ነገሮችን የመካፈልና ችግሮችን በጋራ የመፍታት እሴቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠንካራ አቋም አላቸው፤ ለዚህም በቁርጠኝነት ይሰራሉ ብሏል መግለጫው።

ኦሮሚያ የብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ማእከል ናት፤ የኦሮሞ ህዝብም ሌሎች ብሄሮችን በማቀፍ ይታወቃል ያለው ኦዲፒ፥ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ብሄር ብሄረሰቦችን ለማጋጨት የሚደረጉ ሴራዎችን በማጋለጥ እንደ ትናንቱ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር በመሆን ለሀገር ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል።

ምሁራን እና የመንግስት ሰራተኞችም ከፓርቲው ጋር በመሆን አዳዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅ፣ እንዲሁም የተለያዩ ምርምር እና ጥናቶችን በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ እንዲሁም አሁን የተጀመረው ለውጥ በእውቀት እንዲመራ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።

የፀጥታ አካላት በከፈሉት መስዋእትነት ለውጥ መምጣቱን እና አሁንም ለውጡን ለማስቀጠል ከፍተኛ ስራ እየሰሩ መሆኑን በመጥቀስ፥ በቀጣይም የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ የዜጎች መብት እንዲከበር እንዲሁም ከህዝቡ የተሰጣቸውን እምነትና ሀላፊነት ከህዝብ ጎን በመሆን እንዲወጡ ጥሪውን አቅርቧል።

ለኢህአዴግ እህት እና አጋር ድርጅቶች ባስተላለፈው መልእክትም እርስ በእርስ ስንደማመጥ ለህዝባችን ምሳሌ እንሆናለን፤ ካልተደማመጥን ደግሞ ለህዝባችን ችግር እንፈጥራለን ያለው ፓርቲው፥ የህዝቡን ፍላጉት በማስቀደም እርስ በእርስ በመደማመጥና በመወያየት ለሀገር ግንባታ በጋራ እንስራ ብሏል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በአሁኑ ወቅት እየሰፋ የመጣውን የፖለቲካ ምህዳር በመጠቀም የዴሞክራሲ ስርዓትን መገንባት ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው ብሏል ኦዲፒ።

በተለይም በአሁኑ የሽግግር ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችንና እንቅፋቶችን ለማስወገድ የፖለቲካ ፓርቲዎች መደማመጥ ወሳኝ በመሆኑ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የህዝብን ጥቅም በማስቀደም፣ ህገ መንግስቱን በማክበር እንዲሁም ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ትግል ብቻ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፏል።

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት አሁን በፓርቲው ውስጥ ለመጣው ለውጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን በመግለጽ፥ በቀጣይም ህዝቡ በሚያደርጋቸው ትግሎች ውስጥ በመሳተፍና በመምራት እንዲሁም ለህዝቡ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት፣ ፓርቲውን ለመስበር የሚደረጉ ሙከራዎችን ፊት ለፊት ሆኖ በመጋፈጥ በእውቀት እና በብልጠት በመመከት አሁን የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፏል።

በሙለታ መንገሻ

You might also like
Comments
Loading...