Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በህዋ ሳይንስ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና የፈረንሳዩ ብሄራዊ የስፔስ ጥናት ማዕከል በህዋ ሳይንስ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል።

ተቋማቱ በጋራ ለመስራ የሚስችላቸውን ስምምነት በዛሬው ዕለት መፈራረማቸውንም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ስምምነቱ ከሳተላይት የሚገኙ የአየር ንብረት መረጃዎችንና መተግበሪያዎችን በመጠቀም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን በዘላቂነት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስራዎችን በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው።

የህዋ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እርሻን፤ የደን ሽፋን፤ ውሃ የሚገኝባቸውን አካባቢ መለየትና መከታተል የሚያስችሉ ተግባራትን መከወን የሚያስችል እና ሌሎች ተግባራትንም በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

የሰው ሃይል አቅም ግንባታና የልምድ ልውውጥ፣ የህዋ ሳይንስን ለሰላማዊ ግልጋሎት ለመጠቀም ማዕቀፍ መፍጠር፣ የትብብር መስኮች ወደ ትግበራ የሚገቡበትን ሁኔታዎችን ማመቻቸትም የስምምነቱ አካል ነው።

 

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ እና የፈረንሳዩ ብሄራዊ የስፔስ ጥናት ማዕከል ፕሬዝዳንት ዶክተር ጄን-የቭስ ሊ ጋል መፈረማቸውንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያማለክታል።

You might also like
Comments
Loading...