Fana: At a Speed of Life!

ብሪታንያ የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ለኢትዮጵያ ልትመልስ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሪታንያ ሙዚዬም የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ሊመልስ ስለመሆኑ ተሰማ።

ሙዜየሙ የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ለመመለስ ያሰበው በኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ መሆኑን ገልጿል።

ባለፈው ዓመት ታዲያ የአጼ ቴዎድሮስ ጸጉር በሙዜየሙ ውስጥ እና በኦንላይን ለዕይታ መብቃቱ ብዙዎችን ማስቆጣቱ ይታወሳል።

አጼ ቴዎድሮስ ከ150 ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ 1968 መቅደላ ላይ ለእንግሊዝ ወታደሮች እጅ አልሰጥም በማለት ራሳቸውን መሰዋታቸው የሚታወስ ነው።

ይህንን ተከትሎ ታዲያ ወታደሮቹ የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ጨምሮ በርካታ ነዋየ ቅዱሳት የብራና መጽሐፍትን ዘርፈዋል።

በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጉዳዩ ዙሪያ ለመወያየት ለሐሙስ ቀጠሮ መያዙም ተሰምቷል።

ኤምባሲው የብሪታንያ ሙዚየም እዚህ ውሳኔ ላይ በመድረሱ ምስጋና አቅርቧል።

እንዲሁም የልዑል አለማየሁን አጽም ጨምሮ መጽሐፍትና ሌሎች ነዋያ ቅዱሳት ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ ይችላሉ የሚል ተስፋን አጭሯል።

ለረዥም ጊዜ ያህል የአጼ ቴዎድሮስ ጸጉር በህልፈታቸው ወቅት መቅደላ ላይ ምስላቸውን ካስቀረው ሰዓሊ ቤተዘመዶች ቤት የነበረ ሲሆን፥ በአውሮፓውያኑ 1959 ለሙዜየሙ ስለማበርከታቸውም ይነገራል።

በቅኝ ግዛትና ከዚያም በኋላ የተዘረፉ 90 በመቶ የሚደርሱ የአፍሪካውያን የጥበብ ስራዎች ከአህጉሪቱ ውጪ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

አፍሪካውያን ታዲያ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ወቅቶች የተዘረፉ ንብረቶችን ለማስመለስ  የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ይገኛሉ።

ምንጭ፦ኤፒ

በአብርሃም ፈቀደ

You might also like
Comments
Loading...