Fana: At a Speed of Life!

በጌዴኦ ዞን በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጌዴኦ ዞን በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ በተደራጀ መልኩ ቀጥሏል።

ፋና ብሮድካስቲንክ ኮርፖሬት በስፍራው ባደረገው ቅኝት፥ ካሳለፍነው እሁድ ጀምሮ ተፈናቃዮችን የመለየት እንዲሁም ጎን ለጎንም የእህል፣ የመገልገያ ቁሳቁስና አልባሳት ስርጭት እየተካሄደ መሆኑን ተመልክቷል።

በዚህም አልሚ ምግብ፣ ጥራጥሬ፣ ዘይት፣ ብስኩት እንዲሁም እንደ ብረትድስት እና ጀሪካን ያሉ የመገልገያ እቃዎች እና አልባሳት ለተፈናቃዮች እየቀረቡ ይገኛሉ።

ምግብና ቁሳቁሶቹን የማቅረብ ስራው ከመንግስት፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ከባለሀብቶች፣ ከጌዴኦ ዞን ወጣቶች እና ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር በመተባበር ነው እየተሰራ ያለው።

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያም በዲላ ዙሪያ እና በገደብ ወረዳ ጎቲቲ ቀበሌ ለሚገኙ 20 ሺህ ተፈናቃዮች ለአንድ ወር የሚበቃ እህል ማሰራጨታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከምግብ ስርጭት ባሻገር ከፍተኛ ክፍተት የሚታይበትን የጤና አገልግሎት ለማሟላትም የተለያዩ የጤና ባለሙያዎች ቡድን ችግሮቹ በስፋት ወደሚታይበት ጎቲቲ ወረዳ አቅንተዋል።

በዚህም መሰረት የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አራት ዶክተሮችን ያካተተ 20 አባላት ያሉት የህክምና ቡድን ወደ ስፍራው ልኳል።

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮም በተመሳሳይ የህክምና ቡድን አባላትን ተፈናቃዮች ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች መላኩ ነው የተነገረው።

በቂ የህክምና አገልግሎት ለመስጠትም ህፃናትን፣ ነብሰ ጡር እና የወለዱ እናቶችን የመለየት ስራ እየተከናወነ ሲሆን፥ እስካሁንም ከ12 ሺህ በላይ ህፃናትን እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ ነብሰ ጡር እና የወለዱ እናቶች ተለይተዋል።

በቀጣይ ቀናትም የመለየት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል የተባለ ሲሆን፥ ከዚህ ጎን ለጎን የሚሰጥ የህክምና አገልግሎትም ተጠናክሮ እቀጥላል ነው የተባለው።

ተፈናቃዮቹ በብዛት የሚገኙባቸው አካባቢዎች ያለውን የመጠለያ ችግር ለመቅረፍም ከቀይ መስቀል እና ከተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመሆን እየተሰራ ይገኛል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከአዲስ አበባ ከተማ የተነሱ የበጎ አድራጎት ቡድን የመጠለያ ችግሩን ለማቃለል የሚረዳ 1 ሺህ ሜትር ሸራ በትናንትናው እለት አበርክተዋል።

ፋና ብሮድካስቲንክ ኮርፖሬት በስፍራው በቅኝቱ ወቅት በርካቶች በማህበራዊ ትስስር ግረ ገፆች ፎቶ ግራፏን የተቀባበሉትን ወይዘሮ ሙሉነሽ ኢረታን አግኝቷል።

አሁን ላይ ግን ጎቲቲ ቀበሌ ከሚገኙ ተፈናቃዮች ተለይታ ከእነ ቤተሰቦቿ ወደ ዲላ ሆስፒታል ተወስዳ ህክምና በመከታተል ላይ ትገኛለች።

ወይዘሮ ሙሉነሽ፥ አሁን ላይ በተሻለ ጤንነት ላይ እንደምትገኝ እና በዲላ ሆስፒታል እየተደረገላት የሚገኘው ህክምና እና ሌሎች እንክብካቤዎች ደስተኛ መሆናን ተናግራለች።

በኃይለሚካኤል ዴቢሳ

You might also like
Comments
Loading...