Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይሰፍን የሚፈልጉ ሀይሎችን ከልክ በላይ መታገሱ ዋጋ እያስከፈለ ነው – የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 16 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይሰፍን የሚፈልጉ ሀይሎችን ከልክ በላይ መታገሱ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያናገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መጥተው ለሁሉም በውጭ ለሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ ሲያቀርቡ ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል።

ወደ ሀገር ቤት የገቡትም የለውጥ ሀይሉን ለመደገፍ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ለውጡ እንዳይቀለበስ እና በኢትዮጵያ ያለውን ፌደራላዊ ስርዓት ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የገባው ድርጅታቸው ኦዴግ  በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ለውጥ እንዳለ ያምናል።

በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የለውጥ እሳቤ የተለየ አረዳድ ስላለው እንጂ የሚታይ ለውጥ አለ ይላሉ አቶ ሌንጮ።

የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ አዲስ አበባ የገባው አርበኞች ግንቦት ሰባት የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊው አቶ ኤፍሬም ማዴቦም የለውጥ ሂደት መጀመሩን ይገልጻሉ።

የቀደመው የፖለቲካ ስርአት አግላይ እና በጥቂት ሰዎች ብቻ የበላይነት የሚዘወር መሆኑን የሚያስታውሱት ሃላፊው፥ ይህም በርካቶችን ለስደት መዳረጉን አብራርተዋል።

ባለፈው አመት በተደረገው ለውጥ ግን የጠላት እና ወዳጅ የዘመናት ክፍፍልን ያስቀረ በሽብር የተፈረጁ ድርጅቶች ጭምር እንደ ጠላት ሳይቆጠሩ ወደ ሀገር ቤት የገቡበት ነው ይላሉ አቶ ኤፍሬም።

ድርጅታቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ከነጭራሹ የለም በሚል ሲታገል ቆይቷል የሚሉት አቶ ኤፍሬም፥ አሁን ላይ ምህዳሩ ሰፍቷል ባይባልም ለማስፋት ፍላጎት እና አቅም ያላቸው ሀይሎች ጥረት እያደረጉ መሆኑን መታዘባቸውን ተናግረዋል።

ያለፉት 12 ወራት የፖለቲካው ዘርፍ ስኬቶች እንዳሉት ሁሉ በፈተናዎች የታጀበ መሆኑንም ነው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ የሚናገሩት።

ከለውጡ በኋላ በለውጡ ባለቤትነት እና ተጠቃሚነት ላይ የተፈጠረው ውዝግብ ቀዳሚው ፈተና መሆኑን የአርበኞች ግንቦት ሰባት የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊው አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ገልጸዋል።

የዜግነት ፖለቲካ በኢትዮጵያ መንገስ አለበት በሚለው እና ኢትዮጵያ ውስጥ የብሄር ጥያቄ አልተመለሰምና መፈታት አለበት በሚሉት መካከልም ልዩነቱ እየሰፋ መጥቷልም ነው የሚሉት።

በሁለቱም ወገኖች መካከል ተቀራርቦ ለመነጋገር ፍላጎት አይታይም የሚሉት አቶ ኤፍሬም፥ መንግስት በዚህ ረገድ የበኩሉን መጫወት እንዳለበት ያነሳሉ፤ በሁለቱ ጽንፎች ውጥረት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገውን ለውጥ በፍጥነት ማየት አለመቻሉን በመጥቀስ።

ለችግሮቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸው ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸውም ነው በንግግራቸው ያነሱት።

የኦዴግ ሊቀመንበሩ አቶ ሌንጮ ለታም መንግስት የጀመረውን ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር የመፍጠር ጥረት እንዲገፋበት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከወቀሳ ያለፈ አማራጭን ሊያቀርቡ ይገባል ነው የሚሉት።

አርበኞች ግንቦት ሰባት መንግሰት በሀገሪቱ መረጋጋት እንዳይሰፍን የሚፈልጉ ሀይሎችን ከልክ በላይ ታግሷል የሚል አቋም አለው።

አስፈላጊውን እርምጃ ባለመውሰዱም የህግ የበላይነት እየተሸረሸረ መምጣቱን ይገልጻል።

በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ የቀደመ የሽብር ፍረጃቸውን አንስቶ የጋበዛቸውን ፓርቲዎች ከልክ በላይ መታገሱ ይብቃም ነው ያሉት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊው።

በሁለት ፅንፍ በሚያራምዱት አቋም ለሀገሪቱ መረጋጋት ስጋት የሆኑ ፓርቲዎች ተቀራርበው እንዲመክሩ እና ለህዝብ እና ሀገር ወደሚበጀው አቋም እንዲመጡ መንግስት ሀላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

 

 

በፋሲካው ታደሰ

 

 

       

You might also like
Comments
Loading...