Fana: At a Speed of Life!

32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ እየተካሄደ ነው ።

በስደተኞች፣ ከስደት ተመላሾች እና በውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይ ላይ ትኩረቱን ያደረገው 32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ እየተካሄደ ነው ።

32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ባደረጉት ንግግር ተጀምሯል።

ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግርም በአፍሪካ በኢኮኖሚ፣በማህበራዊ ፣በጤና፣በንግድና ሌሎች ዘርፎች ላይ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል ።

በህብረቱ ጉባዔ ላይ የአህጉሪቱ መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅት መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ባለሀብቶች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች መታደማቸው ነው የተገለፀው።

በወቅቱ ከተገኙት ባለሀብቶች ውስጥም የቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ተባባሪ ሊቀመንበር የሆኑት ቢል ጌትስ ንግግር አድርገዋል።

ቢል ጌትስ በንግግራቸውም ድርጅታቸው በአፍሪካ ሀገራት በተለያዩ ዘርፎች ዙሪያ ውጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአፍሪካ ሀገራት በጤና ፣በመሰረተ ልማት ግንባታ ፣በድህነት ቅነሳ መርሃ ግብር፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳች ዙሪያ በርካታ ስራዎች ማከናወናቸውን ገልፀዋል።

ለዚህም ባለፉት 20 ዓመታት በአፍሪካ ድህነትን ለመቀነስና የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል 50 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ኢንቨስት ማድረጋቸውን አንስተዋል ።

በቀጣይም በአፍሪካ በኢኮኖሚ፣በጤና መሰል ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ የቻሉትን ሁሉ በማድረግ አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል ።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው ድርጅታቸው በአፍሪካ በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ብሎም ኢኮኖሚውን ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም ድርጅቱ ኢኮኖሚን በማሻሻል የጤናውን ዘርፍ ማሳደግ በሚል መርህ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ስለሆነም በጤናው ዘርፍ የሚከሰቱ ችግሮችን ለማስወገድ ችግሮቹ ከተከሰቱ በኋላ የህክምና ከመስጠት ይልቅ ቀደሞ መከላከልና መቆጣጠር የሚሻል መሆኑን አንስተዋል ።

እንደ ምሳሌም በአፍሪካ የተከሰተውን የኢቦላ በሽታ ወረርሽኝ በተቻለው ፍጥነት ለመግታት መሰራቱን ተናግረዋል ።

በመጨረሻም ሀገራት የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጠንካራና ዲሞክራሲያዊ አመራር እንዲፈጥር በማድረግ፣በሀገር ውስጥ ያለውን የኢኮኖሚ ግንባታ በማሳለጥ ለጤናው ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል ።

የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂኣኒ ኢንፋንቲኖ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ስፖርት ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ፣ጤና እና መሰል ጉዳዮችን ለማሻሻል ያለውን አዎንታዊ ሚና አብራርተዋል።

በተለይም ስፖርት የተተኪውን ትውልድ አስተሳሰብና ጤና ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ተናግረዋል ።

ከዚህ ባለፈም ስፖርት የሀገራትን ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ በፆታና ተያያዠ ጉዳዮች ላይ ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ስለሆነም ሁሉም ሀገራት በስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ያላቸውን ስራ አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት ።

በአብርሃም ፈቀደ

You might also like
Comments
Loading...