Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት የበጀት ድጋፍ ረቂቅ ላይ እየተወያየ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት በ2016 በጀት ዓመት የበጀት ድጋፍ ረቂቅ እና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ እየተወያየ ይገኛል፡፡

ከሰሞኑ የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፤ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፤ 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔውን ሲያካሂድ በክልሉ ርእሰ መሥተዳድር የቀረቡትን ሹመቶች ማጽደቁ ይታወሳል፡፡

አዲስ የተቋቋመውና በርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሚመራው የአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት በ2016 በጀት ዓመት የበጀት ድጋፍ ረቂቅ እና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እያደረገ ይገኛል፡፡

በውይይቱ አዲሱ ካቢኔ ቀደም ሲል በክልሉ በፀደቀው በጀት መሰረት  ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ያቀረቡትን መነሻ እቅድ በዝርዝር በማየት የክልሉን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን በሚያግዝ መልኩ የበጀት ድጋፍ ረቂቅን እየተመለከተ ነው፡፡

የመሥተዳድር ምክር ቤቱ ሌላኛው አጀንዳ የ2016 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹ የደረሱበት ደረጃ ነው፡፡

በዚህም መምህራን፣ ርእሳነ መምህራን እና የትምህርት ሱፐርቫይዘሮች የተማሪዎች ምዝገባን በተቀመጠለት የጊዜ መርሐ ግብር በየትምህርት ቤቶቻቸው ተገኝተው እንዲያካሂዱ የሚያስችል ግምገማ አካሂዶ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ አሚኮ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.