Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 89ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ለማቋቋም በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ሲሆን፥ በዚህም ከዚህ ቀደም በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ስር የነበሩና በብረታብረት፣ በአውቶሞቲቭ፣ በእርሻ መሳሪያዎች ምርት፣ የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪና ፕላንት እንዲሁም የፖሊመር ምርት ዘርፎች የተሰማሩትን ተቋማት ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ስር በማደራጀት የሃብት አጠቃቀሙን ውጤታማ ለማድረግ እና ወደ አትራፊነት እንዲሸጋገር ለማስቻል የማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ለውሳኔ ቀርቧል።

ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ የተሰጡ ግብአቶች ተካተው ረቂቅ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል።

በመቀጠልም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በሩሲያ ፌዴሬኝን መካከል የኒኩሌር ሀይልን ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም የተደረገ የትብብር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም ሁለቱ ሀገራት የ1968ቱ የኒኩሌር መሳሪያዎች እሽቅድምድምን የሚከለክለውን ዓለም አቀፍ ስምምነት እና ከዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር የገቡትን ስምምነት ባከበረ መልኩ የኒኩሌር ኢነርጂን ለሰላማዊ ዓላማዎች ጥቅም ላይ ማዋላቸው በሀገራቱ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን በመግለፅ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የማጽደቂያ ረቂቅ አዋጁን አዘጋጅቶ አቅርቧል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.