Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ፡፡

ፕሬዚዳንቷ የቱኒዚያ ፕሬዚዳንት ቤጂ ካይድ ኢሴብሲ፣ የኢስቶኒያ ፕሬዚዳንት ክርስቲ ካልጁሌይድን፣ የዓለም የምግና የእርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ግራዚያኖ ዳ ሲልቫንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቬሮኒካ ሚሸል ባችሌት ጄርያን ዛሬ ከሠዓት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ኢትየፖጵያ ከቱኒዚያ ጋር የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንዳላት ያነሱት ፕሬዚዳንቷ ሁለቱ ሀገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ግንኙነት በቀጣይነትም የበለጠ ለማጠናከር ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ከኢስቶኒያ ፕሬዚዳንት ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከኢስቶኒያ ጋር በቅርበት ተባብራ መስራት እንደምትፈልግና መንግስትም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ወደ ተግባር የሚሸጋገርበትን መንገድ ያመቻቻል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ አስረድተዋል፡፡

በዚሁ ውይይታቸው ፕሬዚዳንት ካልጁሌይድ ኢስቶኒያ በዲጂታል ቴክኖሎጅ ያላትን የዳበረ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማጋራት ዝግጁ መሆኗን ማረጋገጣቸው ነው የተገለጸው፡፡

የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ የሀገሪቱ የቅድሚያ ትኩረት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ግንባር ቀደም መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል።

አያይዘውም ከሀገሪቱ ፍላጎትና የፖሊሲ አቅጣጫዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ድርጅቱ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

የዓለም የምግና የእርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ግራዚያኖ ዳ ሲልቫ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የድርጅቱ የረጅም ጊዜ አጋር መሆኗን በመጥቀስ በቀጣይነት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ተገቢውን ድጋፍ እንሰጣለን ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቬሮኒካ ሚሸል ባችሌት ጄርያ፥ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን ለማስከበር በምታደርገው ጥረት የዜጎችን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስልጠናዎችን በመስጠትና ተቋማትን ለመገንባት ለምታደርገው እንቅስቃሴ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለፃቸውን ከፕሬዚዳንት ጽሀፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like
Comments
Loading...