Fana: At a Speed of Life!

ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከቻይና የውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ቼን ዚያንዶንግ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት2፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከቻይና የውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ቼን ዚያንዶንግ ጋር ተወያዩ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የቻይና የውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትርና የቻይና አፍሪካ ፎረም የክትትል ኮሚቴ ሊቀመንበር ሚስተር ቼን ዚያንዶንግ በጽህፈት ቤታቸው ተቀበለው በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ዶክተር ወርቅነህ በዚህ ውይይታቸው የቻይና እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ሁሉን አቀፍና በሁኔታዎች የማይለዋወጥ በሁለቱ አገሮች ህዝቦች ዘላቂ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ታሪካዊና ረጅም ዘመናትን ያቆጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ተጠቃሚነትለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።

ሚስተር ቼን ዚያንዶንግ በበኩላቸው የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት ሁሉን አቀፍ ስትራቴክ ትብብር መሆኑን በመግለጽ ይህንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ቻይና ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ላይ ትገኛለች ብለዋል።

በተያያዘ ዜና ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማዘመን እየተደረገ ባለው ርብርብ የዓለም የጤና ድርጅት እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አድንቀዋል።

ትብብሩ ከዚህ በበለጠ ተጠናከሮ እንደሚቅጥል እምነታቸው መሆኑንም ዶክተር ወርቅነህ ገልጸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው በአትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የተመዘገበውን ውጤት አድንቀዋል።

ድርጅቱ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋገጠዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ከተመሰረተበት ከ 1940 ዓ.ም ጀምሮ የድርጅቱ የረዥም ጊዜ አባል በመሆን በመስራት ላይ ትገኛለች።

You might also like
Comments
Loading...