Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ከተባበሩት አረብ ኢሜሪቶች የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከተባበሩት አረብ ኢሜሪቶች የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ሪም አል ሀሽሚን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ወቅትም ዶክተር ወርቅነህ፥ የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሜሪቶች ግንኙነት በደም የተሳሰረ፣ በጠንካራ መሰረት ላይ የተጣለ እና ታሪካዊም ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን የእስልምና እምነት ተከታዮች ተቀብላ በማስተናገድ ከመካከለኛው ምስራቅና ከአረብ ሀገሮች ጋር ቀደምት ግንኙነት የመሰረተች ግንባር ቀደም አገር ናትም ብለዋል።

ሁለቱ ሀገሮች የህዝባቸውን ጥቅምና ደህንንት ለማስጠበቅ በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፥ ይህንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በልዩ ትኩረት ይሰራልም ብለዋል።

የተባበሩት አረብ ኤሜሪቶች ለኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እና ለኢትዮጵያዊያን ዜጎች እየተደረገ ላለው ድጋፍም ዶክተር ወርቅነህ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሪም አል ሀሽሚ በበኩላቸው፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር በኢትዮጵያ የመጣውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ አድንቅዋል።

የተባበሩት አረብ ኤሚሪቶች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ቁርጠኛ ናት ያሉ ሲሆን፥ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍም አጠናክራ ትቀጥላለች ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

You might also like
Comments
Loading...