Fana: At a Speed of Life!

የ1 ኢትዮጵያዊ ዓመታዊ የስጋ ፍጆታ 7 ኪሎ ግራም ሲሆን፥ ካደጉት ሀገራት አንጻር ሲታይ በ10 እጥፍ ያንሳል

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድም በሌላም መንገድ ስጋ የመመገብ ልምድን ለማቆም የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ይስተዋላል።

በብሪታንያ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ሰዎች ስጋን በምግብነት ለመጠቀም ማቆም ወይንም ለመቀነስ ማሰባቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሆኖም የስጋ ፍጆታ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመርን እንጂ መቀነስን ሲያሳይ አልታየም፤ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ከ50 ዓመታት በፊት ከነበረበት ከ70 ሚሊየን ቶን በ2017 ወደ 330 ሚሊየን ቶን ዕድገት ማሳየቱ ነው።

በርግጥ የምርቱ በዚህ መልኩ መጨመር በ960ዎቹ 3 ቢሊየን የነበረው የህዝብ ቁጥር በአሁኑ ወቅት ወደ 7 ነጥብ 6 ቢሊየን መድረሱ፣ መካከለኛ ገቢ ያለው ህዝብ መጨመሩ፣ የዓለም አማካይ የገቢ መጠን በሦስት እጥፍ መመንደጉ በምክንያትነት የሚነሱ ስለመሆናቸው ባለሙያዎቹ ይጠቅሳሉ።

በቅርብ ዓመታት በተደረገ ጥናት ታዲያ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ኒውዝላንድና አርጀንቲና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመታዊ የስጋ ፍጆታቸው ቁጥር የመጀመሪያዎቹን ደረጃዎች ተቆናጠዋል።

ሀገራቱ ዓመታዊ የስጋ ፍጆታቸው በግለሰብ 100 ኪሎ ግራም ሲሆን፥ ይህም ከ50 ዶሮዎች ጋር ይተካከላል።

አብዛኛዎቹ ያደጉት ሀገራት ዓመታዊ የስጋ ፍጆታቸው የተሻለ ሲሆን፥ ደሀ ሀገራት በአንጻሩ ፍጆታቸው እጅግ አነስተኛ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱ መካከልም የኢትዮጵያውያን ዓመታዊ የስጋ ፍጆታ 7 ኪሎ ግራም ሲሆን፥ ይህም ከአማካይ የአውሮፓውያን ፍጆታ አንጻር ሲታይ በ10 እጥፍ ያንሳል።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ ወደ መካከለኛ ገቢ ከገቡ ሀገራት መካከል የሆኑት ቻይናና ብራዚል የስጋ ፍጆታቸው በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር አሳይቷል።

በህንድ አብዛኛው ህዝብ አትክልት ተመጋቢ ነው ተብሎ ቢታመንም ነገርግን ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው ህዝቧ ስጋ ተመጋቢ መሆኑን ጥናቶች አሳይተዋል።

ሆኖም በዓመታዊ የስጋ ፍጆታዋ ከዓለም እጅግ አነስተኛ ከሚባሉት ሀገራት ውስጥ የምትመደብ ሲሆን፥ ዓመታዊ የስጋ ፍጆታቸው በግለሰብ አራት ኪሎ ግራም ብቻ መሆኑ ተገልጿል።

ባላደጉት ሀገራት ውስጥ ገበታቸው ላይ የፍጆታው አነስተኛ መሆን ከስጋ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም ያስቀራል፤ ባደጉት ሀገራት ደግሞ የፍጆታው ከፍተኛ መሆን የጤና ጉዳቶችን ማስከተሉ አልቀረም።

ባለሙያዎቹ አንድ ግለሰብ መጠነኛ የሆነ የስጋ አመጋገብ ካለው ለጤና መሻሻል የራሱን አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ይመክራሉ።

 

ምንጭ፦ቢቢሲ

በአብርሃም ፈቀደ

You might also like
Comments
Loading...