Fana: At a Speed of Life!

የመንግስትና የኦነግ የእርቀ ሰላም የቴክኒክ ኮሚቴ ወደ 22 የኦሮሚያ ወረዳዎች ሊሰማራ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የእርቀ ሰላም የቴክኒክ ኮሚቴ በኦሮሚያ ክልል 12 ዞኖች ወደሚገኙ 22 ወረዳዎች ሊሰማራ መሆኑ ተገለፀ።

የእርቀ ሰላም የቴክኒክ ኮሚቴው በዛሬው እለት ለስምሪቱ እያደረገ ባለው ዝግጅት እና አስካሁን ባከናወናቸው ስራዎች ዙሪያ በኦሮሞ ባህል ማእከል መግለጫ ሰጥቷል።

የቴክኒክ ኮሚቴው በመግለጫው፥ እስካሁን የተከናወኑ የእርቅ ስራዎች እንዲሳኩ የክልሉ መንግስት እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለዋል።

የእርቀ ሰላም የቴክኒክ ኮሚቴው ከነገው እለት ጀምሮም በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ወደሚገኙ 22 ወረዳዎች እንደሚሰማራም ነው ያስታወቀው።

የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ በመግለጫው፥ የመንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የእርቀ ሰላም የቴክኒክ ኮሚቴ እያከናወነ ያለውን የእርቅ ተግባር ወደ መጠናቀቁ ደርሷል ብለዋል።

የእርቀ ሰላም የቴክኒክ ኮሚቴው ለስራ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ወደሚገኙ 22 ወረዳዎች ይሰማራል ያሉት አባ ገዳ በየነ፥ አሁን ያለው የእርቅ ስራ ወደ አንድ አቅጣጫ እየመጣ መሆኑንና መንግስት እና ኦነግ ለእርቁ በቁርጠኝነት ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ተወካይ አቶ ሞገስ ኢዳአ “መንግስት እርቅ ይፈልጋል፤ ለእርቅም ይሰራል” ያሉ ሲሆን፥ እርቁ እንዲሳካ መንግስት አፍፈላጊውን ድጋፍ በሙሉ ያደርጋል ብለዋል።

“የኦነግ ሰራዊት ትጥቁን ለአባ ገዳዎች አስረክቦ ወደ ካምፕ ሲገባ እኛም እንደ መንግስት የሚጠበቅብንን ሀላፊነት እንወጣለን” ያሉት አቶ ሞገስ፥ ወደ ካምፕ የሚገባው ሰራዊትም እንደ ፍላጎቱ ስልጠና ወስዶ እንዲሰማራ ይደረጋል ነው ያሉት።

የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳም፥ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ምሁራንን እና የሀገር ሽማግሌዎችን ያካተተው የእርቀ ሰላም የቴክኒክ ኮሚቴ እርቁ የተሳካ እንዲሆን ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል።

የኦነግ ሰራዊትን በተመከለከተ፥ በጫካ ያለው የኦነግ ሰራዊነት ሀላፊነት በአባ ገዳዎች እና በእርቀ ሰላም የቴክኒክ ኮሚቴ እጅ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የኦነግ ሰራዊት ትጥቁን ለአባ ገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች በማስረከብ ወደ ካምፕ ይገባል ብለዋል።

71 አባላት ያለው የእርቀ ሰላም የቴክኒክ ኮሚቴ ከነገ ጀምሮ ወደ ክልሉ ወረዳዎች ይሰማራል ያሉት አቶ ዳውድ፥ በጫካ ያለው የኦነግ ሰራዊትም የኮሚቴውን ውሳኔ ተቀብሎ ስራ ላይ እንዲያውል መልእክት አስተላልፋለሁ ብለዋል።

የቴክኒክ ኮሜተው አባላት በበኩላቸው፥ የኦነግ ሰራዊት ከየካቲት 14 2011 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሶስት ቀናት ማለትም ማክሰኞ፣ ረቡዕ እና ሀሙስ ቴክኒክ ኮሚቴዎቹ ጋር እየተመዘገበ ትጥቁን ለአባ ገዳዎች እና ሀደ ሲቂዎች እያስረከበ ወደ ካምፕ ይገባል ብለዋል።

የኦነግ ሰራዊት ወደ ካምፕ የሚገባባቸው ሶስት ቀናትም በሰላማዊ መልኩ እንዲጠናቀቅ ከሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ጋር ከስምምነት መደረሱን አስታውቋል።

የኦነግ ሰራዊት ወደ ካምፕ ከገባ በኋላም የእርቀ ሰላም የቴክኒክ ኮሚቴው ሰራዊቱ ያሉበትን ሁኔታ እንደሚከታተል አስታውቋል።

በሙለታ መንገሻ

You might also like
Comments
Loading...