Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ አንጻር ቀሪ ስራዎች አሉ – አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ለማድረግ አሁንም ሊሠሩ የሚገቡ ቀሪ ስራዎች መኖራችውን የድቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ክልላዊ የትምህርት ጉባኤ ሲጀመር ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፣ በክልሉ አሁንም የትምህርት ገበታን ያልተቀላቀሉ ህፃናት ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።

የሀገራዊና ክልላዊ ምዘናዎች ውጤት ዝቅተኛ መሆን እና የትምህርት ቤቶች ምቹ አለመሆን ወይም ከደረጃ ዝቅ ያሉ መሆን ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊቀረፉ የሚገቡ ችግሮች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በክልሉ በተለያየ ምክንያት የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን ለመጠገን እና መጽሐፍት የማቅረብ ጥረቶች መደረጋቸውንም አውስተዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጌታሁን ጋረደው በበኩላቸው፥ የትምህርት ዘመኑ በብዙ ምክንያቶች ሲደነቃቀፍ መቆየቱን ገልጸዋል።

ህፃናትን ለፓለቲካዊ ጥቅም እንደማያዣ አድርጎ እንዳይማሩ ማድረግ በመጭው ህይወታቸው ላይ የተፈፀመ ፍርደ ገምድልነት መሆኑንም አንስተዋል።

ከ2010 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በክልሉ በነበረው አለመረጋጋት በበርካታ ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱንም ጠቅሰዋል።

በክልሉ በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ቅበላ ከእቅድ በታች መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም በቅድመ መደበኛ 47 ነጥብ 5፣ በመጀመሪያ ደረጃ 79 ነጥብ 6 ሲሆን፥ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ 71 ነጥብ 1 በመቶ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

 

በታደሰ ሽፈራው

You might also like
Comments
Loading...