Fana: At a Speed of Life!

በዓለም የጤናማ ሀገራት ደረጃ ስፔን የመሪነቱን ቦታ ያዘች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለም የጤናማ ሀገራት ደረጃ አውሮፓዊቷ ስፔን በአንደኛ ደረጃ ተመርጣለች።

ስፔን በዚሁ ዘርፍ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2017 ስድስተኛ ደረጀ ላይ የነበረች ሲሆን፥ ዘንድሮ አምስት ደረጃዎችን አሻሽላ ነው የመሪነቱ ቦታ ላይ የተቀመጠችው።

ደረጃው ይፋ የተደረገው የብሉምበርግ ሄልዚየስት ኔሽን የፈረንጆቹ 2019 ዕትም ላይ ነው።

የውድድሩ መስፈርቶችም አማካይ የመኖሪያ ዕድሜ፣ ውፍረት፣ ሲጋራ ማጨስን እንዲሁም ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘትና ሌሎችም ይገኙበታል።

ሁለተኛዋ ጤነኛ ሀገር የተባለችው ጣልያን ስትሆን፥ በ2017ቱ ምርጫ የመጀመሪያው ደረጃ ላይ እንደነበረች ይታወሳል።

አይሳላንድ፣ ጃፓን እና ስዊዘርላንድ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፤ ብሪታንያ 19ኛ፣ አሜሪካ 35ኛ፣ ቻይና 52ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በርግጥ መስፈርቱ ብዙ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን፥ ከነዚህ ጉዳዮች መካከልም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆነ በሽታዎች ስርጭት ከመግታት አንጻር ያሳዩት መቆጣጠርም አንዱ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የአመጋገብ ስርዓት በተመለከተ ስፔንና ጣልያን ከመሪነት ቦታ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል።

ለዚህም እንደምክንያት የተቀመጠው በሽታ በመከላከል የሚታወቁት የባህር ምግቦችንና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ምግቦችን በማዘውተራቸው መሆኑ ተጠቅሷል።

በውድድሩ አፍሪካን ጨምሮ 169 ሀገራት የተካተቱ ሲሆን፥ ከ30ዎቹ የሰሃራ በታች ሀገራት መካከል 27 የሚሆኑት ደረጃውን አላሟሉም ወይንም ጤነኛ አይደሉም ተብሏል።

ሆኖም ከነዚህ ሀገራት መካከል ሞሪሸየስ 72ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ከጤነኛ ሀገራት ተርታ ተመድባለች።

ምንጭ፦ ብሉምበርግ

በአብርሃም ፈቀደ

You might also like
Comments
Loading...