Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የተሰራው በአካል ላይ የሚደርስ ጉዳት መጠን መለኪያ መተግበሪያ የሙከራ ስራ ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የተሰራው አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአካል ጉዳተኝነት መጠን መለኪያ መተግበሪያ የሙከራ ስራ ሊጀምር ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተመራማሪዎች ያሰራው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአካል ጉዳተኝነት መጠን መለኪያ መተግበሪያ እና ብሄራዊ መመሪያ የሙከራ ስራ ለማስጀመር ርክክብ ተደርጓል፡፡

ከዚህ በፊት የአካል ጉዳተኝነት መጠን ልኬት በዘልማድ የሚከናወን በመሆኑ በአደጋ ጊዜ በሚከፈል ካሳ መጠን ላይ በፍርድ ቤቶችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍተኛ አለመግባባቶች ይፈጠሩ ነበር።

ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ በሆኑ አደጋዎች ተጠቂ የሆኑ ሰዎች የደረሰባቸው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነና ምን ያህል ለአካል ጉዳተኝነት እንደዳረጋቸው አስልቶ የሚያስቀምጥ መሆኑም ተገልጿል።

ይህ በአለም ላይ አዲስ የሆነው ቴክኖሎጂ ከተሞከረ በኋላ በሀገሪቱ የህክምና ማዕከላት ወደ ስራ እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሹመቴ ግዛው ተናግረዋል፡፡

ቴክኖሎጂው በሀገር ውስጥ የስራ እድል ከመፍጠር በዘለለ ለሌሎች ሀገራት በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንደሚረዳም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ‹‹ኦርቶፔዲክስና ትራማቶሎጂ›› ማህበር ጋር ወደ ፊት አብሮ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like
Comments
Loading...