Fana: At a Speed of Life!

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተፈጠረ ግጭት በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

አዲስ አበባ፣ጥር 30፣201 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች ውስጥ በተፈጠረ ግጭት በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በአካባቢው የተከሰተውን ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክቶ የአማራ ክልል የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።

ዳይሬክተሩ በመግለጫቸውም  በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች ውስጥ በአማራ እና ቅማንት ብሄረሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት በበርካታ ሰውና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በተፈጠረው ግጭት በርካታ መኖሪያ ቤቶች በእሳት የተቃጠሉ መሆኑንና በዚህም አያሌ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ነው የገለጹት።

ግጭቱም በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ልዩነት በመፍጠር አካባቢውን የግጭት ቀጠና ለማድረግ  አቅደው በሚሰሩ ሃይሎች አማካኝነት የተፈጠረ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

አነዚህ ሃይሎችም በሺዎች ሚቆጠሩ በርካታ ከባድ መሳሪያዎችን በህገ ወጥ መንገድ በማስገባትና ለዚሁ እኩይ አላማ ላሰለጠኗቸው አካላት በማስታጠቅ በንጹሃን ዜጎች ህይወት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አንስተዋል።

ግጭቱ እንደገና ያገረሸበት ምክንያትም አካባቢውን ለማረጋጋት ተሰማርቶ የነበረው 24ኛ ክፍለ ጦር ወጥቶ 33ኛ ክፍለ ጦር ለግዳጅ ሊገባ ሲል ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም በአካባቢው  የተደራጁ ቡድኖች  በጸጥታ አካላት ላይ ጥቃት በማድረሳቸው ነው ብለዋል ።

በመሆኑንም የክልሉ መንግስት በንፁጹሃን ዜጎች ላይ በደረሰው የህይወት መጥፋትና  ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ ፥ጉዳት ለደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች  አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን  አቶ አሰማኸኝ ተናግረዋል ።

በቀጣይ በአካባቢው ያለውን አለመረጋጋት ወደ ነበረበት ለመመለስም  የክልሉ መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት  እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ መሰረትም ከግጭቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው በሚል የተያዙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውንና የእሥር ማዘዣ ወጥቶባቸው እተፈለጉ ያሉ መኖራቸውንም  ተናግረዋል፡፡

እስካሁንም በምዕራብ ጎንደርና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት 39 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውንም አቶ አሰማኸኝ አስረስ ተናግረዋል ።

 

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like
Comments
Loading...