Fana: At a Speed of Life!

የዝውውር ጭምጭምታዎች

አዲስ አበባ ፣ ጥር 14 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓውያኑን አዲስ አመት መግባት ተከትሎ በተከፈተው የጥር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ክለቦች ክፍተታቸውን ለመሸፈን እየተንቀሳቀሱ ነው።

እስካሁን ባለው ሂደት በትልቅ ደረጃ የሚወራ ዝውውር ባይኖርም አንዳንድ ክለቦች የተወሰኑ ተጫዋቾችን አዘዋውረዋል።

የካታላኑ ክለብ ባርሴሎና ባልተጠበቀ ሁኔታ ፕሪንስ ቦዓቴንግን በውሰት ውል ወደ ካምፕ ኑ አዘዋውሮታል።

ባርሴሎናዎች ወደ ሲቪያ የሸኙትን ሙኒር ኤል ሃዳዲን ቦታ ለመሸፈን በማሰብ ቦዓቴንግን ማስፈረማቸውን አስታውቀዋል።

የትናንቱ ዝውውር ለቦዓቴንግ በተጫዋችነት ዘመኑ 10ኛ ክለቡ ሆኖ ተመዝግቦለታል።

በሌላ በኩል አሽሊ ኮል ወደ እንግሊዝ በመመለስ በቀድሞ የክለብ አጋሩ ፍራንክ ላምፓርድ ለሚሰለጥነው ደርቢ ካውንቲ ፊርማውን አኑሯል።

ሃሪ ኬንን በጉዳት ያጣው ቶተንሃም ሆትስፐርስ በበኩሉ የአንዲ ካሮልን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን ጋርዲያን ዘግቧል።

ከእሱ በተጨማሪም ሌሎች የአጥቂ አማራጮችን ክለቡ እያማተረ ነው ተብሏል።

የማንቼስተር ዩናይትዱ አማካይ ፖል ፖግባ ደግሞ በኮንትራት ስምምነት ዙሪያ ከክለቡ ለመነጋገር ዝግጁ ስለመሆኑ የተለያዩ የእንግሊዝ ጋዜጦች ዘግበዋል።

ፈረንሳዊው አማካይ ከሞሪንሆ መውጣት በኋላ በክለቡ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋች መሆን ችሏል፤ በክለቡ ባለው ቆይታም ደስተኛ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው።

ከፖግባ በተጨማሪም አንቶኒ ማርሻል ከላንክሻየሩ ክለብ ጋር ያለውን ኮንትራት ለማራዘም ስለመስማማቱም ተነግሯል።

ቀያይ ሰይጣኖቹ ወጣቱን አማካይ ስኮት ማክቶሚኒን ተጨማሪ ውል ማስፈረማቸው ይታወሳል።

ክለቡ በክረምቱ ቋሚ አሰልጣኙን ከመቅጠሩ በፊትም የክለቡን እግር ኳስ ዳይሬክተር ለመሾም እንቅስቃሴ ላይ ስለመሆኑም ተሰምቷል።

የሰሜን ለንደኑ አርሰናል ደግሞ ሃሜስ ሮድሪጌዝን በውሰት ውል የማስፈረም ፍላጎት አለው እየተባለ ነው።

በአንጻሩ የተጫዋቹ ባለቤት ሪያል ማድሪድ ኮሎምቢያዊውን አጥቂ ለቶተንሃም ሊሸጠው እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኤሲ ሚላኑ አጥቂ ጎንዛሎ ሂጉዬን ወደ ምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ የሚያደርገው ዝውውር እስካሁን ፍጻሜውን አላገኘም።

ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ማውሪዚዮ ሳሪ የክለቡን የአጥቂ ችግር ለመቅረፍ አርጀንቲናዊውን አጥቂ ማስፈረም ቢፈልጉም፤ ጉዳዩ በሚላን በኩል እልባት አላገኘም።

ኤሰ ሚላኖች ሂጉዬንን ለመልቀቅ ምትክ እስከሚያገኙ ድረስ ጉዳዩ በእንጥልጥል እንደሚቆይም ገልጸዋል።

አሁን ላይም የጀኖዋውን አጥቂ ክርዚስቶፍ ፒያቴክን ለማስፈረም እየተነጋገሩ ስለመሆኑ ቱቶ ስፖርትን ዋቢ ያደረገው የኢቭኒንግ ስታንዳርድ እና ጋርዲያን ዘገባ ያመላክታል።

በአንጻሩ የሂጉዬን ዝውውር የሚሳካ ከሆነ አልቫሮ ሞራታ ወደ አትሌቲኮ ማድሪድ እንደሚያመራ እየተነገረ ነው።

የፒ ኤስ ጂው አማካይ አድሪያን ራቢዮት ከክለቡ ጋር አዲስ ኮንትራት አልፈራረምም ማለቱን ተከትሎ የፓሪሱ ክለብ ተጫዋቹን ከተጠባባቂ ቡድኑ ጋር ልምምድ እንዲያደርግ ማድረጉ ይታወሳል።

ክለቡ ተጫዋቹ በርካታ ክለቦች እየፈለጉት መሆኑን ተከትሎ ወራት የቀረውን ኮንትራት አላራዝምም በማለቱ ነበር ይህን ያደረገው።

የፈረንሳይ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካልም ክለቡ ውሳኔውን በማንሳት ለተጫዋቹ ተገቢውን ቦታ እንዲሰጠው ጥሪ አቅርቦለታል።

 

 

ጋርዲያን፣ ደይሊ ሜይል፣ ቢቢሲ፣ ስካይ ስፖርት እና ኢቭኒንግ ስታንዳርድ የመረጃዎቹ ምንጮች ናቸው።

 

You might also like
Comments
Loading...