Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በአቶ ገላሳ ዲልቦ ከሚመራው የኦነግ አመራሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 02፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በአቶ ገላሳ ዲልቦ ከሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

በአቶ ገላሳ ዲልቦ የሚመራው የኦነግ የአመራር ቡድን መንግስት ያደረገለትን ጥሪ ተከትሎ ነው ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሀገር የተመለሰው።

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳም በዛሬው እለት በአቶ ገላሳ ዲልቦ በሚመራውን ቡድን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ወቅት ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፥ “የተደረገላችሁን ጥሪ ተቀብላችሁ በመካከላችን በመገኘታችሁ ለእኛ ትልቅ ደስታ ነው” ብለዋል።

“ሁላችንንም ከቤት ያስወጣን ለኦሮሞ ህዝብ ትግል ነው፤ የኦሮሞ ህዝብ የጋራ ሀብታችን ነው” ያሉት አቶ ለማ፥ “ነባር አመራሮች ሲያደርጉት ለነበረው ትልግ ከእኛ ዘንድ ከፍተኛ ምስጋና ይቸራቸዋል” ሲሉም ተናግረዋል።

“ተለያይተን ብንቆይም ዛሬ አንድ ላይ ተቀምጠን መነጋገራችን እና አብሮ ለመስራት መስማማታችን ለኦሮሞ ህዝብ ትግል ትልቅ ተስፋን የሚሰጥ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

የኦሮሞ ህዝብ አሁን ያገኘውን ድል ወደ ቀጣይ ምእራፍ ለማሸጋገር መደጋገፍ እና አብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ርእሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

አሁን ከገተኘው ድል ህዝቡ ጥቅም እያገኘ ነው ያሉት ርእስ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፥ ይሁን እንጂ ብዙ እንቅፋቶች አሉ፤ ይህንንም በብስለት እና በመደጋገፍ ማለፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

በአቶ ገላሳ ዲልቦ በሚመራ የቀድሞ የኦነግ አመራሮችም ከጎናቸው በመሆን የኦሮሞን ህዝብ ትግል ወደ ቀጣይ ምእራፍ እንደሚያሸጋግር እምነት እንዳላቸውም ገልፀዋል።

አቶ ለማ በንግግራቸው፥ “እኛ ከእናንት ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን፤ ለኦሮሞ ህዝብ ይበጃል የምትሉትን ምክር በሙሉ ከእናንተ ለመቀበል ዝግጁ ነን፤ በኦሮሞ ህዝብ ትግል ውስጥ ታላላቅ በመሆናችሁ ከእናንተ ጋር መስራት ኩራት እንዲሰማን ያደርጋል” ብለዋል።

የኦነግ አመራር አቶ ገላሳ ዲልቦ በበኩላቸው፥ “ዛሬ በመካከላችሁ በመገኘታችን ታላቅ ደስታ ይሰማናል” ሲሉ ተናግረዋል።

“እኛ የመጣነው ትግል ለማድረግ ነው” ያሉት አቶ ገላሳ ዲልቦ፥ “የምናደርገው ትግል ግን እርስ በእርስ ለመጠላለፍ ሳይሆን ለመደጋገፍ ነው” ብለዋል።

በቀጣይም እጅ ለእጅ በመያያዝ እና በመደጋገፍ የኦሮሞን ህዝብ ትግል ወደ ቀጣይ ምእራፍ ለማሸጋገር እንደሚሰሩም ነው ያስታወቁት።

በሙለታ መንገሻ

You might also like
Comments
Loading...