Fana: At a Speed of Life!

ከተሸከርካሪ ፍሰት የፀዱ የመንገዶች ቀን ነገ እሁድ ጥር 5 ለሁለተኛ ጊዜ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባና በተመረጡ የክልል ከተሞች ከተሸከርካሪ ፍሰት የፀዱ የመንገዶች ቀን ነገ እሁድ ጥር 5 ለሁለተኛ ጊዜ ይካሄዳል።

ከትራፊክ ፍሰት ነፃ መንገዶች ቀን አዲስ አበባን ጨምሮ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ አዳማ፣ ጅማ፣ መቀሌ፣ ጅጅጋ እና ድሬዳዋን እንደሚያጠቃልል ተገልጿል።

የመጀመሪያው ዙር ህዳር 30 መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፥ በአዲስ አበባ የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን በተገኙበት ነበር በይፋ የተጀመረው፡፡

ዶክተር አሚር አማን የነገውን ቀን በማስመልከትም “ሁላችሁም ከቤተሰቦቻችሁ፥ ከልጆቻችሁ ጋር በመሆን እንድትሳተፉ ተጋብዛችኋል” የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል።

የከተማ መንገዶችን በተወሰነ መጠን ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ በማድረግ የሚከናወን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንና አጋላጭ መንስኤዎቻቸውን ለመከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል መርሃ ግብር ነው።

በዚህም መሰረት በወር አንድ ቀን ወሩ በገባ የመጨረሻውን እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተመረጡ መንገዶችን ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ በማድረግ ቦታውን የተለያዩ ጤናን ለሚያበለፅጉ የአካል እንቅስቃሴዎች ለመስራት፣ ጤናማ የአኗኗር ዘዴ መልዕክቶችን ለማስተላለፍና ለተለያዩ የጤና ቅድመ ምርመራ ስራዎችን ለማከናወን ያስችላልም ተብሏል።

በሰባት ከተሞች ላይ ከተሽከርካሪ ነፃ በሆኑ የተመረጡ መንገዶች መርሃ ግብር ሲጀመር የአካል እንቅስቃሴዎች፣ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ነፃ ምርመራዎች እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተከናውነው ነበር።

“ጤናማ የአኗኗር ዘዴ ለጤናማ ህይዎት” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ፕሮግራም እስከ ሐምሌ 30 2011 ዓመተ ምህረት እንደሚከናወን ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወሳል።

 

 

 

You might also like
Comments
Loading...