Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ ሀገራት ከተጠሩ 60 የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ጋር በሚቀጥለው ሳምንት ይወያያሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 03፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተለያዩ ሀገራት ከተጠሩ 60 የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ጋር በቀጣዩ ሳምንት ውይይት እንደሚያካሂዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በውይይቱም እስካሁን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እየተተገበረ ባለው ማሻሻያ ዙሪያ እና ባለፉት 10 ወራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሀላፊነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በተገኙ የዲፕሎማሲ ውጤቶችና በቀጣይ የውጭ ጉዳይ ተልዕኮን በተመለከተ እንደሚወያዩም ተገልጿል።

በተጨማሪም አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ይበልጥ ማስጠበቅ በሚቻልበት ሁኔታ በተለይም ኢትዮጵያዊነት በዓለም መድረክ ጎልቶ እንዲወጣ ከዳያስፖራው ጋር ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው አምባሳደሮች ሆነው እንዲንቀሳቀሱ፣ የዜጎች ክብር የሚረጋገጥበት፣ ብሄራዊ ደህንነታቸው የሚጠበቅበት፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲያችን በሚጎለብትበት ሁኔታ ላይም ይወያያሉ።

በውይይቱ አዳዲስ ተሿሚ እና ነባር አምባሳደሮችን ጨምሮ 60 ሚሲዮን መሪዎች እና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ይሳተፋሉ።

ዛሬ ቀደም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በነበሩት አምባሳደር መለስ አለም ምትክ አቶ ነብያት ጌታቸው መሾማቸው ይታወሳል።

አዲስ የተሾሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በዛሬው እለት በተለያዩ ጉዳዮች ላይም መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ነገ ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም የባህል ቀን እንደሚከበር አስታውቀው፥ በባህል ቀኑ ላይም በአፍሪካ ህብረት የሚገኙ አምባሳደሮች እንዲገኙ ይደረጋል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩም በዋናነት አምባሳደሮቹ አዲስ አበባን አንዲያውቋት እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

 

በስላባት ማናዬና ለይኩን አለም

 

You might also like
Comments
Loading...