Fana: At a Speed of Life!

በአማራና ትግራይ ክልል ክለቦች የሚደረጉ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል-አቶ አሰማኸኝ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራና ትግራይ ክልል ቡድኖች መካከል የሚደረጉ ቀሪ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን በገልተኛ ሜዳ ሳይሆን በእራሳቸው ሜዳ እንዲያደርጉ ዝግጀት መደረጉ ተገለፀ፡፡

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አሰማኸኝ አስረስ ፌዴሬሽኑ ባወጣው መርሃግብር መሰረት ፋሲል ከነማ ወደ መቐለ በመጓዝ ጨዋታውን  የሚያደርግ ሲሆን በተመሳሳይ ስሁል ሽረ ወደ ባሕር ዳር በማቅናት ጨዋታውን እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ክልል ክለቦች ከ2010 ጀምሮ በገለልተኛ ሜዳ  ሲጫወቱ የቆዩ ሲሆን አሁን ግን በክልሎቹ መካከል ስምምነት ላይ በመደረሱ በሜዳዎቻቸው የሚያደርጉ ይሆናል ብለዋል ሀላፊው ፡፡

የአማራና የትግራይ ክልል የስፖርት ኮሚሽን እና የየክልሎቹ ከፍተኛ አመራሮች ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር በደረሱት የጋራ ስምምነት መሰረት ነው ቡድኖቹ ጨዋታዎችን  በሜዳቸው የሚያደርጉት፡፡

የፀጥታ ችግር እንዳይከሰትም  በበቂ ሁኔታ ዝግጅት መደረጉን  አቶ አሰማኸኝ አስረስ ተናግረዋል፡፡

ክለቦቹ ጨዋታዎችን ከሜዳቸው ውጭ ሲያደርጉ በመቆየታቸው ከደጋፊ የሚያገኙትን ገንዘብ እና ድጋፍ ሲያሳጣቸው እንደነበር ገልፀዋል፡፡

አቶ አሰማኸኝ  ስፖርት ሁሉንም ሰላም የሚያደርግ እና የሚያስተሳስር እንጂ ለግጭት የሚዳርግ የፖለቲካ መቀስቀሻ አይደለም ያሉ ሲሆን ስፖርት ከፖለቲካ ነጻ መሆን አለበትም ብለዋል፡፡

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like
Comments
Loading...