Fana: At a Speed of Life!

በምዕራብ ጎንደር ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት በተካተቱበት ቡድን ይጣራል – ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 3 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብ ጎንደር በተነሳ ችግር ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ጉዳይ እንዲጣራ ከውሳኔ ላይ መደረሱን የጦር ሀይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ሃላፊ ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

የጦር ሀይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹምና የዘመቻ ዋና መምሪያ ሀላፊ ጀኔራል ብርሀኑ ጁላ ዛሬ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በወቅቱም በምእራብ ጎንደር በተነሳ የጸጥታ ችግር ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ መከላከያ ንጹሃን ሰዎችን ገድሏል መባሉን ያስተባበሉ ሲሆን ሰራዊቱ በህዝብ ላይ አለመተኮሱን ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይም ሁሉም የሚመለከተው አካል ተካቶበት እንዲጣራ አቋም ተይዞ መወሰኑን ጠቅሰው፥ መከላከያ ወደ ንጹሀን ዜጎች እንዳልተኮሰ የሚያሳይ መረጃ አለን ብለዋል።

ከሰሞኑ ሰራዊቱ ሱር ኮንስትራክሽን በአካባቢው ለሚሰራው ፕሮጀክት ማሽኖችን ለማጓጓዝ የጸጥታ ችግር ያሰጋኛል በማለት በመከላከያ እንዲታጀብ ያቀረበው ጥያቄ ፍቃድ በማግኘቱ የመከላከያ ሰራዊት እንዳጀበው አንስተዋል።

ከዚህ በኋላ ሼኸዲ ከተማ ላይ ህዝቡ ሱር ኮንስትራክሽን ሲበድለን ነበር በማለት እንዲፈተሽ ላቀረበው ጥያቄ ተፈትሾ ይለፍ ከተባለ በኋላ፥ በአካባቢው በነበረና ውሀ ከሚቀዳ የቦቴ መኪና ጋር ባሉ 10 ወታደሮች ላይ ደፈጣ ተደርጎ ጥቃት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

ይህን ተከትሎም መከላከያ እርምጃ ወስዷል ነው ያሉት።

ከዚያ በኋላ ግን ተፈትሾ እንዲያልፍ ተደርጎ የነበረው የሱር ኮንስትራክሽን መሳሪያ እና አጃቢ ወታደሮች እንዲቆሙ ተደርጎ በህዝብ ተከበዋልም ነው ያሉት ጀኔራል ብርሃኑ።

በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉም ከፍታ ቦታን ከያዙ ታጣቂዎች ተኩስ ወደ ህዝቡና አጃቢ ወታደሮች ላይ መከፈቱንም ጠቅሰዋል።

ጀኔራሉ እስካሁን ባለው መረጃ ሰራዊቱ ራሱን ለመከላከል ያደረገው ጥረት እንጅ ወደ ህዝብ አለመተኮሱንም አስረድተዋል።

ሆኖም ደፈጣ ይዞ የተኮሰ ታጣቂን ትቶ ወደ ህዝብ የተኮሰ ወታደር ካለ እንዲጣራ እና አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድበት ተቋሙ ፍቃደኛ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በጥቅሉ በመከላከያ ደረጃ ጎንደር ውስጥ ያለው መረጃ ይሄ መሆኑን በማንሳት ጉዳዩ ሊጣራ እንደሚገባና፥ ሰራዊቱ በማጣራቱ ሂደት ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ተቋሙ ይቅርታ ለመጠየቅና የተጎጂ ቤተሰቦችን ለመካስ ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መከላከያ እንዴት የግል ንብረት ያጅባል ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄም፥ ይህ አዲስ አለመሆኑንና ስጋት እንዳለበት የተረጋገጠ ነገር እስካለ ድረስ መከላከያ ከተጠየቀ እጀባን ያደርጋል ብለዋል፤ ተቋሙ በሆነው ነገርም የተሰማውን ሃዘን ገልጿል።

ጀኔራሉ በትግራይ ክልል በዛላምበሳ እና ሽረ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እየተንቀሳቀሰ እያለ እንቅስቃሴው እንዲዘገይ ስለተደረገበት ሁኔታም ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል።

ጀኔራል ብርሀኑ በጥቅሉ የፖለቲካ ነጋዴዎች ወጣቶች ላይ ተጽእኖ አሳርፈው ያደረጉት ነገር መሆኑን ጠቅሰው፥ በዛላምበሳና ሽረ ወታደሩ እየወጣ እያለ ወጣቶቹ ስጋት አለን ጎረቤት ይወረናል የሚል ጥያቄ አንስተው መከላከያም ጥያቄያቸውን መስማቱን አስታውሰዋል።

ነገር ግን ትክክለኛ ጥያቄው የወጣቶቹ ሳይሆን ከኋላ ሆኖ የሚገፋቸው ሀይል መኖሩንና የወጣቶቹን ድርጊት የክልሉ አስተዳደር እንደማያምንበትም ገልጸዋል።

እርምጃ ያልተወሰደውም ለሀገሪቱ ሰላም መልካም ስላልሆነና የጥያቄው ምንጮችም ወጣቶች ስላልሆኑ ነው ብለዋል።

ከወጣቶቹ ጋር በተደረገ ውይይትም ይህንን ማረጋገጣቸውን ጠቁመው፥ ወጣቶቹ የገፋፏቸውን ግለሰቦች በስም እየጠቀሱ ይቅርታ መጠየቃቸውንም አውስተዋል።

በወቅቱ የመከላከያ ሰራዊት አጣዳፊ ነገር ስለሌበት በስፍራው መቆየቱንና ሌላው ተልዕኮ ቢኖረው ግን እርምጃው የተለየ ይሆን እንደነበርም አንስተዋል።

አሁን ላይ መከላከያ አዲስ አሰፋፈርን እየተከተለ ስላለ እና ከኤርትራ በኩል ምንም አይነት የጦርነት ስጋት ስለሌለ መከላከያ ከስፍራው እንደተንቀሳቀሰም ገልጸዋል ።

ከምእራብ ኦሮሚያ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያም እንደ ቄለም ወለጋና ሆሮ ጉድሩ አይነት ዞኖች ውስጥ፥ በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ ሸኔ ቡድን መንግስትን የማታለል ስራ በመስራቱ የፀጥታ ችግር መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

ኤርትራ የነበረው በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ኢትዮጵያ ሲገባ 1 ሺህ 200 ወታደሮቹን ለመንግስት ቢያስረክብም፥ ሃገር ውስጥ ያለውን ታጣቂ ትጥቅ ያስፈታል ተብሎ ቢጠበቅም አዲስ የማሰልጠን ሂደት ውስጥ በመጀመር ጸረ ህዝብ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል።

መንገድ መዝጋት፣ ለድሀና ሀብታም ኮታ እየሰጠ ገንዘብ መሰብሰብ፣ የክልሉን የወረዳና ዞን መዋቅር ማፍረስና የመንግስት መሳሪያን ከግምጃ ቤት የመዝረፍ ስራ መስራቱንም ነው የተናገሩት።

መንግስት በዚህ ጊዜ በሚያውቋቸውና ሰዎችና በሽማግሌዎች ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ መጠየቁን አስታውሰው፥ ኦነግ ግን ይህን ጊዜ መግዣ ማድረጉን አውስተዋል።

ከዚህ በኋላም መንግስት ወደ እርምጃ በመግባቱ የፈረሱ የመንግስት መዋቅሮች መልሰው እየተቋቋሙ መሆኑንና የተዘረፉ መሳሪያዎች እየተመለሱ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ከተሞቹም ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እየተመለሱ መሆኑንና ንግድም እየተጀመረ መሆኑን አንስተው፥ አሁን ላይ የሸኔ ሀይሎች ወደ ጫካ በማፈግፈጋቸው ሰራዊቱ እየተከተለ እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ገልጸዋል።

 

 

 

በካሳዬ ወልዴ

 

 

 

You might also like
Comments
Loading...