Fana: At a Speed of Life!

ለጥምቀት በዓል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ገለፀ

ዲስ አበባ፣ ጥር 03፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለጥምቀት በዓል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ገለፀ።

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ የበዓል ዝግጅቱን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጥምቀት በዓል በጎንደር በልዩ ሁኔታ እንደሚከበር ያነሱት ምክትል ከንቲባው፥ በሀገር ውስጥ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጥምቀትን በጎንደር እንዲያከብሩ ጥሪ ሲደረግ መቆየቱን ገልፀዋል።

በዚህም በርካታ እንግዶች ወደ ጎንደር ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ከአሜሪካ ጎንደር 17 ቀጥታ የአውሮፕላን በረራዎች እንደሚኖሩ አመልክተዋል።

በዓሉ መንፈሳዊና ትውፊታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር እና እንግዶቹም ቆይታቸው የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊው የፀጥታና የአገልግሎት ዝግጅት ተደርጋል ብለዋል።

የከተማዋ ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅም እየሰሩ ናቸው ብለዋል።

ከበዓሉ በፊት ባሉ ቀናት የአካባቢው ትውፊትና ባህል የሚያስተዋወቅ የባህል ሳምንት እንደሚኖር ተናግረዋል።

ስርዓተ ጠምቀቱ የሚፈፀምበት መዋኛ ገንዳንም ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ተግባር ተከናውኗል።

ወደ ጎንደር ከሚመጡ የአካባቢው ተወላጆች እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚካሄድም ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል።

በዓሉ በፍቅር፣ መተሳሰብና አብሮነት  ስሜት እንዲከበር እየተሰራም እንደሆነ ነው ያመለከቱት።

 

በነብዩ ዮሃንስ

 

You might also like
Comments
Loading...