Fana: At a Speed of Life!

ሀገር ዓቀፍ የጥራት ሽልማት በብሔራዊ ቤተ መንግስት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 6ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት በብሄራዊ ቤተ መንግስት ተካሄደ፡፡

በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ በሀገሪቱ ያሉ ተቋማት ጥራትን መሰረት አድርገው እንዲሰሩና በዓለምአቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መንግስት አበክሮ ይሰራል ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ ጥራት የስነልቦና የበላይነትና የስልጣኔ መገለጫ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ገጽታ ግንባታ ከሚኖረው አወንታዊ ፋይዳ አንጻር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አንስተዋል፡፡

መንግስት ከኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ጋር አብሮ መስራቱን እንደሚቀጥልም ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራቱ በበኩላቸው፥ የሽልማቱ ዓላማ በሀገሪቷ ያሉ አምራቾችና አገልግሎት ሰጭዎች እንዲሁም በግንባታው ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ለጥራት የሚያደርጉትን ስራ በማበረታታት እውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ድርጅቱ ያስቀመጠውን ዓለም አቀፍ መስፈርት ያሟሉ ድርጅቶችና ተቋማትን ሸልሟል ነው ያሉት፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው በኢትዮጵያ የጥራትና ተወዳዳሪነት አስፈላጊነት እስካሁን በሚፈለገው መጠን ግንዛቤ ባለመኖሩ ለሽልማቱ በቂ ተወዳዳሪ ማግኘት አለመቻሉንም ጠቅሰዋል።

በዚህ ዓመት 330 የሚሆኑ ድርጅቶች እንዲወዳደሩ ጥሪ መደረጉን የጠቀሱት ስራ አስፈጻሚው፥ ይሁን እንጅ 40 ድርጅቶች ብቻ ፈቃደኛ ሆነው እስከመጨረሻው መዝለቃቸውን አስረድተዋል።

ተቋሙ የጥራትን ጽንሰ ሐሳብ ለማስረጽ ከ11 ዓመታት በፊት በ2000 ዓመተ ምህረት መመስረቱ የሚታወስ ነው፡፡

በስነ ስርዓቱ ላይ 23 ለሚሆኑ ተቋማትና ድርጅቶች ሽልማት የተቀበሉ ሲሆን፥ የጎንደር ዩኒቨርስቲ፣ በላይአብ ኬብል፣ ሀረር ቢራ ፋብሪካ ከተሸላሚዎቹ መካከል ይገኙበታል፡፡

ሽልማቱ ያለባቸውን ክፍተት አሟልተው እና ያላቸውን መልካም ነገር አጎልብተው በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ብርታት እንደሚሆናቸው ተሸላሚ ተቋማት ገልጸዋል፡፡

You might also like
Comments
Loading...