Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ኤድስ ቀን እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ኅዳር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)”የማኅበረሰብ መሪነት ለላቀ ኤች አይ ቪ መከላከል”በሚል መሪ ቃል የዓለም ኤድስ ቀን እየተከበረ ይገኛል።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው መርሐ-ግብር ÷ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰን ጨምሮ በዘርፉ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ፣ አምባሳደሮች ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመርሐ-ግብሩ የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ÷ በኢትዮጵያ እየተከበረ በሚገኘው የዓለም ኤድስ ቀን ማኅበረሰቡ ስለ ቫይረሱ ያለው ግንዛቤ የበለጠ አድጎ ለማስተማር እንዲበቃና በመከላከሉ ረገድ የመሪነት ድርሻውን እንዲይዝ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ቃል የምንገባበት ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው ÷ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 610 ሺህ 350 ሲሆን 61 በመቶ ያህል የቫይረሱ ተጠቂዎች ሴቶች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ባለፈው ዓመት በኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 8 ሺህ 257 ነው።

በፈረንጆቹ 2010 ከነበረው የ 1 ነጥብ 26 በመቶ የሥርጭት ምጣኔ አንፃር ሲታይ 2022 ወደ 0 ነጥብ 9 በመቶ መቀንስ ተችሏል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተወካይ ዶ/ር ፍራንኮይስ ንዳይሽምዬ ÷ የኢትዮጵያ መንግሥት ማኅበረሰቡ ከኤች አይ ቪ ኤድስ እራሱን እንዲከላከል ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ እያደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ ሥራ አድንቀዋል።

በቀጣይም ኅብረተሰቡ ራሱ በመሪነት የመከላከል ሥራዎችን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ሆሴ ማሲንጋ በበኩላቸው ÷ የአሜሪካ ሕዝብ እና መንግስት ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል እስከ አሁን ከ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም አመርቂ ውጤቶች እንደተመዘገቡ አስረድተዋል።

በቀጣይም ከኢትዮጵያ መንግሥት ፣ ጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ከኤች አይ ቪ ኤድስ ነፃ ዓለም መፍጠር ይገባልም ነው ያሉት።

በ2030 ኤች አይ ቪ ኤድስ ለማኅበረሰብ ሥጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ሁሉም አካል ድርሻውን ሊወጣ ይገባል ተብሏል።

የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን ሲከበር በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ36ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ ነው፡፡

በታሪኩ ወልደሰንበት

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.