Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጅቡቲን ሊጎበኙ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ   ጅቡቲን ሊጎበኙ መሆኑ ተገለፀ።

የጅቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  በትናትናው ዕለት  ይፋ እንዳደረጉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በቅርቡ ሀገሪቱን ይጎበኛሉ ብለዋል።

ሁለቱ ሀገራት በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ በመካከላቸው የነበረውን ልዩነት ለመፍታት በከፍተኛ መሪዎች ደረጃ ግንኙነት ሲያደርጉ እንደቆዩ ነው የተጠቆመው።

መሪዎቹ የሚገናኙበት ቀን እንዳልተቆረጠ የተገለፀ ሲሆን፥ ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች  በየሀገራቶቻቸው ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጅቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሃመድ አሊ ዮሱፍ አስታውቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኤርትራ አቻቸው ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ገልጸው ፥  በሀገራቱ መካከል መተማመንን ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ቀንድ  ሰላምና ብልፅግናን ለማምጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የእርቅ ሂደቱን ማስጀመራቸውን በመግለፅ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በጣም ተለዋዋጭ መሆኑን ያነሱት ሚኒስተሩ፥ ከሌሎች የአፍሪካ ክፍሎች በበለጠ ግጭት የሚበረክትበት  መሆኑን  ከአናዶሉ ጋር በነበራቸው ቆይታ  አንስተዋል።

ሚኒስትሩ ሀገራቱ በአንድ ላይ እድሎችን በጋራ ማየት እንዲችሉ፣ እንዲያቅዱ እና ለአካባቢው ህዝብ ተጠቃሚነት በጋራ እንዲሰሩ  ራዕይ ያለው መሪ እንደሚያስፈልግ  ተናግረዋል።

ኤርትራና ጅቡቲ ከፈረንጆቹ 1980 ጀምሮ በመሬት ይገባኛል ምክንያት ውጥረት ውስጥ መቆየታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከዚህ ባለፈ በፈረንጆቹ 2008 የኤርትራ ጦር ወደ ጅቡቲ ግዛት መግባቱን ተከትሎ የሶስት ቀናት ጦርነት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

 

ምንጭ፥አናዶሉ

በኤፍሬም ምትኩ

You might also like
Comments
Loading...