Fana: At a Speed of Life!

ፓሊስ በያሬድ ዘሪሁን፣ በተስፋዬ ኡርጌና ሜ/ጄነራል ክንፈ ላይ የጠየቀውን 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፍርድ ቤቱ በያሬድ ዘሪሁን፣ በተስፋዬ ኡርጌና ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ ፓሊስ የጠየቀውን 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

ተጠርጣሪዎቹ በዛሬው እለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ነው የቀረቡት።

ፍርድ ቤቱ በያሬድ ዘሪሁን ላይ ከህዳር 26 2011 ጀምሮ ታሳቢ የሚሆን የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

እንዲሁም በተስፋዬ ኡርጌ ላይ ፍርድ ቤቱ ከህዳር 24 2011 ጀምሮ ታሳቢ የሚሆን የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

ፖሊስ ቀድሞ በተሰጠው ጊዜ ከተጠርጣሪዎች ጋር ተያያዥ የሆነ ማስረጃ እየሰበሰበ በመሆኑና የሚቀረው ስራ በመኖሩ በዋስ ቢወጡ ማስረጃ እንደሚያጠፉ ስለታመነበት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜው ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል ተብሏል።

የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጉዳይ የተመለከተው ፍርድ ቤት ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀን የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለታህሳስ 10 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በተመሳሳይ የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘውን ጉዳይ የተመለከተው ፍድር ቤት ለተጨማሪ ምርመራና ለቀሪ ስራ ማጠናቀቂያ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀን ፈቅዷል።

ይህም ከህዳር 24 ጀምሮ የሚቆጠር ሲሆን፥ ለታህሳስ 4 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዛሬው የችሎት ውሎ የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ጠበቆች በመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ላይ ሃሳብ እናቀርባለን ብለው የነበረ ቢሆንም ሳያቀርቡ ቀርተዋል።

ፍርድ ቤቱ ከሜቴክ ሰራተኞች ጋር ተመሳጥረው ከሁለት የውጭ ድርጅቶች የድለላ ፍቃድ ሳይኖራቸው ከተገዛ 2 ሺህ 500 ትራክተር 15 ሚሊየን ብር ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በተባሉት አቶ ረመዳን ሙሳ ላይ ለፖሊስ 14 ቀን በመፍቀድ ለታህሳስ 10 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ከዚህ ባለፈ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ከፍተኛ አመራር የነበሩት ዶክተር ሃሺም ቶፊቅ ባለቤት ወይዘሮ ዊዳድ አህመድ ላይ ፖሊስ ባቀረበው ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ማፍራት ምርመራ ከእንይ ሪል እስቴት ያገኘውን መኖሪያ ቤት ማሳገዱንና ለተለያዩ ተቋማት ደብዳቤ መጻፉን ገልጾ ሰነዶችን ለመሰብሰብ 14 ቀን ጠይቋል።

የወይዘሮ ዊዳድ ጠበቃ በበኩሉ የፓሊስ ምርመራ ወደ ተለያዩ ተቋማት ደብዳቤ መላካቸውን የሚያመላክት በመሆኑ ይህን ለመሰብሰብ 14 ቀን መጠየቃቸው አግባብ እንዳልሆነና ደንበኛቸው በዋስ ቢወጡ የሚያሸሹት ማስረጃ የለም በማለት ዋስትና ጠይቀዋል።

ግራና ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤትም የዶክተር ሀሺም ቶፊቅ ባለቤት ወይዘሮ ዊዳድ አህመድ በ60 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ የወሰነ ሲሆን፥ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከባድ በመሆኑ ከአገር እንዳይወጡ የጉዞ እግድ ተላልፎባቸዋል።

መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው የሰባት ቀን የጊዜ ቀጠሮ ውስጥ እሰራለሁ ያለውን ስራ አልሰራም ፣ ፖሊስን የሚፈልገው ቀሪ ማስረጃ ለማግኘት የተጠርጣሪዋ ተጽዕኖ የለም እና ተጠርጣሪዋ በራሳቸው የወንጀል ተሳትፎ እንጂ በሌሎቸው ተጠርጣሪዎች ምክንያት በእስር ማቆየት አይገባም ብሏል ችሎቱ።

በሙስና በተጠረጠሩት ጋዜጠኛ ፍጹም የሽጥላ ፣ ትግስት ታደሰ እና ቸርነት ዳና ላይ ፖሊስ ቀደም ብሎ በተሰጠው ምርመራ ጊዜ የሰራውን በርካታ ስራ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ የትግስት ታደሰ ጉዳይ የተመለከተ ሲሆን፥ ፖሊስ በስሟ በርካታ ሃብት እንደተገኘ እና በህገወጥ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ በማድረግ መጠርጠሩን ገልጿል።

መሪማሪ ፓሊስ በወይዘሮ ትዕግስት ታደሰ ላይ የህብረት ማኒፋክቸሪንግ ማሽን ግንባታ ሶስት ሙያተኞችንና ለተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት የሸጡ ሁለት ምስክሮችን ቃል መቀበሉንና ሌሎች ስራዎችን መስራቱን ለችሎቱ አስታውቋል።

በተጠርጣሪዋ ቤት ምርመራ መደረጉንና በህገ ወጥ መንገድ የተገኙ ገንዘቦችን ህጋዊ አስመስለው የሰሯቸው ስራዎች የሚያሳዩ ሰነዶችን ማግኘቱን ገልጿል።

ጋዜጠኛ ፍፁም የሺ ጥላ ላይም የአራት ሰዎች የምስክር ቃል መቀበሉን፣ ክፍያ እንዲፈፀም የተደረገበት ማስረጃ መሰብሰቡን ፓሊስ የገለፀ ሲሆን፥በሶስተኛ በአቶ ቸርነት ዳባ ላይም የሁለት የምስክር ቃል እንደተቀበለ፣ በድለላ የተከፈላቸውን ኮሚሽን መጠን የሚያሳይ ማስረጃ መሰብሰቡን እና ግለሰቡ በስኳር ኮርፖሬሽን ላይ ህጋዊ ፍቃድ ሳይኖራቸው የሰሯቸው ስራዎች እየመረመርን እንደሆነ በማንሳት ለሁሉም 14 ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።

የትዕግስትና የፍፁም ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው፥ ፓሊስ ቀረኝ ያላቸው ስራዎች ተጨማሪ ጊዜ የሚያሰጡ አይደሉም እና ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ወጥተው ምርመራው ሊቀጥል ይችላል ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

የሶስተኛ ተጠርጣሪ የአቶ ቸርነት የግል ጠበቃ በበኩላቸው ፥የድለላ ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው እና በተመሳሳይ በስኳር ኮርፖሬሽን በህጋዊ መንገድ የድለላ ስራ የሰሩ ሲሆን፥ ፓሊስ ቀረኝ ያለው ምርመራ ከእሳቸው ጋር የሚያገናኘው ነገር ስለሌለ ዋስትና ይፈቀድላቸው ሲል ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ የፓሊስን የዋስትና መቃወሚያ ካዳመጠ በኋላ የምርመራ መዝገቡን ነገ ጠዋት ተመልክቶ 5 ሰዓት ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like
Comments
Loading...