Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ በሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ በሶስት መዝገቦች ክስ የመመስረቻ 10 ቀን ሰጠ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) መርማሪ ፖሊስ በቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ እያጣራ ካለው 18 መዝገብ ውስጥ የሶስቱን ምርመራዬን አጠናቅቄያለሁ ሲል ለአቃቤ ህግ አስረክቧል።

መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ ባቀረበው ማመልከቻ ላይ ከ18 ጉዳዮች ውስጥ ከሶስቱ ውጭ ያሉትን 15 ጉዳዮች አስመልክቶ መዝገቡ እንዲዘጋ አልያም ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በግልጽ ያቀረበው ጥያቄ የለም።

መርማሪ ፖሊስ በሶስቱ መዝገቦች አቃቤ ህግ ክስ ለመመስረቻ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ ስለማይቀር በዛ በሚፈቀድለት ጊዜ ውስጥ የቀሩትን መዝገቦች ምርመራ አጠናቅቃለሁ ሲል፥ በማመልከቻው ከመጥቀሱም ባለፈ ስለ ጉዳዩ አቃቤ ህግ ለችሎቱ እንዲያስረዳም ጠይቋል።

በመርማሪ ፖሊስ የቀረበውን ማመልከቻና ተጨማሪ ሃሳብ የተመለከተው ችሎቱም የተጠርጣሪ ጠበቆች በማመልከቻው ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡ ዕድል ሰጥቷቸዋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆችም አቃቤ ህግ የክርክሩ አካል ባልሆነበት በጉዳዩ ላይ የሚከራከርበት፣ የሚሰየምበትና አስተያየት የሚሰጥበት የህግ አግባብ የለም ብለዋል።

መርማሪ ፖሊስ እያጣራ ያለውን ሁሉንም ጉዳይ አለመጨረሱን ጠቅሶ እያለ መዝገብ ተከፋፍሎ ለአቃቤ ህግ አይላክም፤ ስለዚህ ለአቃቤ ህግ በይፋ ምርመራየን አጠናቅቄ አስረክቤያለሁ ካለም ካሁን በኋላ መርማሪ ፖሊስ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን አስመልክቶ የሚመረምረው ጉዳይ የለውም በማለት፥ ፖሊስ በማመልከቻው ላይ ዋስትና ይከልከሉ ብሎ ስላልጠየቀ ደንበኛችን በዋስ ይውጡልን ሲሉ ዳኝነት ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ እያጣራን ያለነው 18 መዝገብ እንደመሆኑ ሶስቱን ጨርሰናል ማለት ሁሉንም ጨርሰናል ማለት አይደለም ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

እየተጣራ ያለው የሙስና ወንጀል እንደመሆኑና የሙስና ወንጀሎችን ምርመራ በበላይነት የሚከታተለው አቃቤ ህግ በመሆኑ በችሎቱ የመሰየም መብት አለውም ብሏል።

ከዛም ባለፈ በሶስት መዝገቦች ላይ የክስ መመስረቻ ማመልከቻውን ለማቅረብ መሰየሙ ከግምት ገብቶ የጠበቆች አቃቤ ህግ መሰየምና መከራከር የለበትም የሚለው ሃሳብ ውድቅ ይደረግልኝ ሲል ጠይቋል።

የዋስትና ጉዳይ በማመልከቻው ላይ ባለመጠቀሱም ተጠርጣሪው በዋስ ይውጡ መባሉን የተጠረጠሩበት ጉዳይ ዋስትና ስለሚከለክል ሃሳቡን እንቃወማለን ብሏል ፖሊስ።

የግራ ቀኙን ያዳመጠው ችሎቱም በሶስቱ ዳኞች አማካኝነት ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ መርማሪ ፖሊስ እየመረመረ ካለው 18 ጉዳይ ውስጥ ሶስቱን በማጠናቀቁና ለአቃቤ ህግ በማስረከቡ፥ አቃቤ ህግ የመሰየም መብት አለው ብሏል።

ነገር ግን መርማሪ ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ባለመጠየቁ የምርመራ ጉዳይ ታልፏል፤ አቃቤ ህግም የክስ መመስረቻ ማመልከቻውን ለችሎቱ እንዲያቀርብ ተጠይቆ አቃቤ ህግ ማመልከቻውን አቅርቧል።

በማመልቻው መሰረትም በሶስት መዝገቦች ማለትም 1ኛ አባይ ወንዝና አቢዮት ለተባሉ ሁለት መርከቦች ያለ አግባብ ለግዥ፣ ለጥገና፣ ለአስተዳደራዊ ወጪና ለሽያጭ በሚል 545 ሚሊየን 483 ሺህ 103 ብር ያለ አግባብ እንዲወጣ በማድረግና ሃገር ላይ ጉዳት በማድረስ።

2ኛ ከሪቬራ ኢንተርናሽናል ሆቴልና ፒ ቪ ሲ ፕሮፋይል ማምረቻ ግዥ ሲፈጸም ከግዥ መመሪያ ውጭ ግዥው እንዲፈጸም ትዕዛዝ በመስጠት ያለ አግባብ 202 ሚሊየን 882 ሺህ 885 ብር ያለ አግባብ እንዲባክን በማድረግ እንዲሁም 3ኛ የኢምፔሪያል ሆቴል ግዥ እንዲፈጸም ትዕዛዝ በመስጠት ለሆቴሉ ግዥና ጥገና በሚል ያለ አግባብ 103 ሚሊየን 809 ሺህ 755 ብር እንዲባክን በማድረግ በአጠቃላይ ተጠርጣሪው ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር በመሆን በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ ሲካሄድባቸው ቆይቶ ምርመራው በመጠናቀቁ ለክስ መመስረቻ 10 ቀናት እንዲሰጠው አቃቤ ህግ ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው የክስ መመስረቻ ሪፖርት በደረሳችሁ 15 ቀናት ውስጥ ክስ የመመስረቻ ውሳኔያችሁን አሳውቁ እንደሚል ጠቅሰው፥ አቃቤ ህግ 10 ቀናት ይሰጠኝ ሲል መጠየቁ በእጅ አዙር ለሌሎች መዝገቦች ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እየጠየቀ ነው ያለው ስለዚህ ሊፈቀድ አይገባም በማለት ተከራክረዋል።

ከዛም ባለፈ ተጠርጣሪው ከ10 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ ወንጀል እንደሚከሰሱ ጠቅሶ ዋስትና ይነፈግ ማለት እንደማይችልና፥ ጅምር የምርመራ መዝገቡን ችሎቱ አይቶ ያንን መወሰን አለበት በማለትም መከራከሪያቸውን አቅርበዋል።

ከዚህ ባለፈም ቀድሞ ክስ መስርቶና ወስኖ መምጣት እንደማይገባ በመጥቀስ፥ አቃቤ ህግ ቀድሞ ሲከታተለው የነበረ ጉዳይ በመሆኑ በሶስት ቀናት ውስጥ ክስ መመስረት አለበት በማለት ለክስ መመስረቻ 10 ቀን መጠየቅ የለበትም ሲሉም ተቃውመዋል።

አቃቤ ህግ በሶስት መዝገቦች ክስ እመሰርታለሁ ያለው ክሶቹ የቀረውን ጉዳይ ለመመርመር እንደመያዣ ሊጠቀምበት ስለሆነም የጠየቀው ጊዜ ሊፈቀድለት አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።

አቃቤ ህግ በበኩሉ የይርጋ ውሳኔ እስካልተላለፈ ድረስ አቃቤ ህግ የምርመራ ሂደትን መከታተልና መምራት ይችላል፤ ክስ ተመስርቶም ጎን ለጎን የምርመራ መዝገቦችን መከታተል እንደሚችል ጠቅሷል።

10 ቀን የጠየቅነው ለሌላ ሳይሆን ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር ጉዳዩን አብሮ ለማስኬድ መልካም በማሰብ ነው ሲልም ለችሎቱ አስረድቷል።

የግራ ቀኙን ያዳመጠው ችሎቱም አንድ ግለሰብ በሙስና በመጠርጠሩ ብቻ ዋስትና ስለሚነፈግ በጠበቆች በኩል ዋስትና ይፈቀድልን በሚል የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።

አቃቤ ህግ 10 ቀናት መጠየቁም የተጠርጣሪውን መብት የሚያሰፋ እንጂ የሚያጠብ ባለመሆኑ በጠበቆች 10 ቀን መጠየቅ የለበትም በሚል የቀረበውን መከራከሪያ ውድቅ በማድረግ፥ አቃቤ ህግ በ10 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰርት የጠየቀው 10 ቀናት ተፈቅዶለት ለጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

 

ባባሃሩ ይድነቃቸው

You might also like
Comments
Loading...