Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ ከዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ፕሬዚዳንት ቦርጌ ብርንዴ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ፕሬዚዳንት ቦርጌ ብሪንዴ ጋር ተወያዩ።

የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ፕሬዚዳንት ቦርገ ብሬንደ አሁን ላይ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አድንቀዋል።

በመጭው ጥር ወር 2011 ዓ.ም በዳቮስ ስዊዘርላንድ በሚካሄደው የአለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዲሳተፉ ግብዣ አቅርበውላቸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመጭው ጥር ወር 2011 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ዳቮስ በሚደረገው የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ስብሰባ ላይ መሳተፍ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የማሻሻያ ስኬቶችና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስተዋወቅ ዕድል እንደሚፈጥር ቦርጌ ብርንዴ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን የለውጥ ሂደት የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍ የገለጹት የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ፕሬዚዳንቱ ሀገሪቱ በቅርቡ በጀመረችው የለውጥ ሂደትም አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተከናወነ ስላለው የማሻሻያ እንቅስቃሴና በቀጠናው ስለተፈጠረው የሰላም ሁኔታ ሰፊ ማብራሪያ እንደሰጧቸው፥ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like
Comments
Loading...