Fana: At a Speed of Life!

ግጭት ወደተከሰተባቸው ስፍራዎች የምርመራ ቡድን በመላክ አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ እየሰራሁ ነው- ጠቅላይ አቃቤ ህግ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ግጭት ወደተከሰተባቸው ስፍራዎች የተደራጀ የምርመራ ቡድን በመላክ አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ

ጠቅላይ አቃቤ ህግ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ፥ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የያዘውን ቁርጠኛ አቋም ከግብ እንደሚያደርስም አስታውቋል።

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አቅደው ግጭቶችን ቀስቅሰው ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀል፣ ከፍተኛ የንብረት ጉዳት እና የሰብአዊ መብት ጥሰት እያደረሱ የሚገኙ አካላትን የህግ የበላይነትንና የዜጎችን ድህንነት ለማረጋገጥ ሲባል ችግሩ ወደተከሰተባቸው ስፍራዎች የተደራጀ የምርመራ ቡድን በመላክ የምርመራ ሥራ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነባቸው ይገኛል ብሏል።

በዚህ  ህገ ወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት እንዲሁም የወንጀል ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ፣ የግጭቶቹ ዋነኛ ጠንሳሾችና ተዋናዮችን ለህግ ለማቅረብ የሚሰራው ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመግለጫው ያስታወቀው።

በቀጣይም የተገኙ ውጤቶችን ለህዝቡ የሚያሳውቅ መሆኑንም ገልጿል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመግለጫው አያይዞም፥ ህዝቡ በፍትህ ስርዓቱ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመፈታት የማያቋርጥ የአሰራር ስርዓትና የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ መልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ወደማይቀለበሰበት ደረጃ ለማድረስና የፍትህ ስርዓቱን አሰራር ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርቷል።

ለአብነትም በቅርቡ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በህግ ጥላ ስር የዋሉት አካላት የለውጡ ጅማሮ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ ብሏል።

እርምጃው በርካታ የሀገሪቱን ህዝቦች ያስደሰተና ይበል የሚያስብል ተግባር እንደሆነ መረዳት እንደተቻለም ነው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያስታወቀው።

ሰለሆነም የህግ የበላይነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ ተፈጥራ የማየት፣ እኩልነት የተረጋገጠባት ሀገር መገንባትና በፍትህ ስርአቱ ከህግ ውጭ የሆኑ ተግባራት ሲፈጸሙ ፈጻሚው አካል በብሄሩ፣ በሀይማኖቱ እና በማንነቱ ሳይሆን በሰራው ወንጀል ልክ ህግን ማእከል ያደረገ ተጠያቂነት በማስፈኑ ረገድ እየሰራም እንደሚገኝም ገልጿል።

በቀጣይም በተደራጁ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ ሙስናና ሌብነት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲሁም መሰል ተግባር ላይ የተሳተፉ ሕገ-ወጦችን ወደ ህግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ይህ ተግባር አገሪቱ ላለችበት ለውጥ ወሳኝነቱ የጎላ በመሆኑ መንግስት ይህንን አካሔድ ተከትሎ ከህግ ውጭ የሆኑ አካላት ለሚፈጽሙት ተግባር የማይታገስና ለድርድር የማይቀርብ መሆኑንና ተጠያቂ እንድሆኑም ሌት ተቀን ይሰራል ብሏል።

የሀገሪቱ ህዝቦች ይህንን በጎ ተግባር በመደገፍና ከለውጡ ጎን በመሆን መንግስት እያካሄደ ያለውን የህግና የፍትህ የሪፎርም ስራ በመደፈገፍ ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመጸየፍ ሀገሪቱን የሚጎዱ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ወንጀል ፈጻሚ አካል የትኛውም ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ጾታ የማይወክል መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ በማሰገባት በወንጀል ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሕግ እና በሕግ ስርዓት ብቻ የሚዳኙ መሆናቸውን አረጋግጧል።

You might also like
Comments
Loading...