Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ ከኦስትሪያ መራሄ መንግስት ሴባስቲያን ከርዝ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኦስትሪያ መራሄ መንግስት ሴባስቲያን ከርዝ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
 
መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ፥ ኢትዮጵያ ከኦስትሪያ ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነት በአዲስ መንፈስ አጠናክራ እንደምትቀጥል የገለጹ ሲሆን፥ ቬና የኢትዮጵያ የጥንት ወዳጅ ናት ብለዋል።
 
አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ቬናም የአውሮፓ የዲፕሎማሲ መናኸሪያ በመሆናቸው የሁለቱ ግንኙነት አህጉራዊ ተልዕኮም እንዳለው ተናግረዋል።
 
የሀገራቱ ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት እያካሄደች ላለው የለውጥ መስመር ጠቃሚ ነው ብለዋል።
 
የመራሄ መንግስቱ ጉብኝትም በኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቴክኖሎጂ ልውውጥ ዙሪያ መልካም ዕድሎችን እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውውይታቸው ሁሉም በውጭ ሀገራት የነበሩ የፓለቲካ ፓርቲዎች ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን በማንሳት መንግስት የሚያራምደው የለውጥ አጀንዳ በዋናነት ዲሞክራሲያዊ ምርጫን ለማካሄድ ያለመ ነው ብለዋል።
 
ይህም በሀገሪቱ መረጋጋትን በማምጣት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አርዓያ እድትሆን ያድረጋታል ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት።
 
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ይህንንም ኢትዮጵያ ኢምባሲዋን በቬና መክፈቷ ሊያፋጥነው እንደሚችል ጠቁመዋል።
መራሄ መንግስቱ ሰባስቲያን ኩርዝ በበኩላቸው ፥በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥና ለውጡን ተከትሎ ለተስተዋለው የዲሞክራሲያዊ ግንባታና የኢኮኖሚ ለውጥ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
 
ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በአርዓያነት እንደምትጠቀስ የገለፁ ሲሆን፥ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል እንደምትፈልግ ተናግረዋል።
 
ከዚህ በተጨማሪ በአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ገልፀዋል።
 
ሰባስቲያን ከርዝ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
 
መራሂ መንግስቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ሲደርሱ የክብር አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
 
መራሄ መንግስት ሰባስቲያን ከርዝ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በጀርመን በርሊን በተካሄደው የቡድን 20 ሀገራት ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ተገናኝተው ነበር።
 
በተገናኙበት ወቅትም የሁለትዮሽ ስብሰባ ያደረጉ ሲሆን፥ ሀገራቱ የጋራ ግንኙነታቸውን ለማጠንከር በትብብር እንደሚሰሩ መስማማታቸው ይታወሳል።
 
Photo: Office of the Prime Minister-Ethiopia
You might also like
Comments
Loading...