Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ሀገራት አዲስ ዓመታቸውን ተቀበሉ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም ሀገራት አዲስ ዓመታቸውን በተለያዩ ዝግጅቶች ተቀብለዋል።

በፓሲፊክ ውቅያኖስ የሚገኙ ደሴቶች አዲሱን 2019 በመቀበል ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ፥ ሳሞኣ እና ኪሪቢቲ ደሴቶች እንዲሁም ኒውዚላንድ አዲሱን አመት በተለያዩ ዝግጅቶች ተቀብለውታል።

በኒውዚላንድ በተለያዩ አካባቢዎች በጭፍራና ባለቀለም ርችቶችን በመተኮስ አዲሱን የ2019 ዓመት ተቀብለዋል።

አውስትራሊያውያንም በሲድኒ ከተማ በደማቅ ስነ ስርዓት አዲሱን አመት የተቀበሉ ሲሆን፥ በዋና ከተማዋ ሲድኒም ለረጅም ደቂቃ የቆየ አስደናቂ የርችት ትእይነት ቀርቧል።

የብሪታኒያዋ ለንደንም በተለያዩ የሙዚቃ ድግሶች እንዲሁም ከስምንት ቶን የተዘጋጀ እና ከሶስት አቅጣጫዎች በተተኮሰ ርችት ነው አዲሱን ዓመት በደማቅ ሁኔታ የተቀበለችው።

የአሜሪካዋ ኒውዮርክ ከተማ ነዋሪዎች ደግሞ በከባድ ዝናብ ውስጥ ሆነው ወደ ታይም ስኩዌር በመውጣት አዲሱን ዓመት በደማቅ የርችት ስነ ስርዓት እና በሙዚቃ ድግስ ተቀብለዋል።

የፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ነዋሪዎች እና ከተማዋን ለመጎብኘት የሄዱ የውጭ ሀገር ዜጎችም በከተማዋ ቻምፕ ኤሊስስ በመውጣት አዲሱን ዓመት የተቀበሉ ሲሆን፥ በከተማዋ አመፅ ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ከፍተኛ ጥበቃ እንደነበረም ተነግሯል።

ጎረቤት ሀገር ኬንያ ናይሮቢም አዲሱን 2019 በተለያዩ ዝግጅቶች እና የርችት ስነ ስርዓት ተቀብላለች።

የተባበሪት አረብ ኢሚሬቶቿ ዱባይም በየዓመቱ ተጠባቂ የሆነውን ደማቅ የርችት ትእይንት በማቅረብ አዲሱን ዓመት የተቀበለች ሲሆን፥ ከቡርጀ ከሊፋ ህንፃ ላይ የተተኮሱ ርችቶችም የበርካቶችን ቀልብ ስቧል ነው የተባለው።

ከዚህ ባለፈም እስያዊቷ ሰሜን ኮሪያን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገራትም አዲሱን 2019 ዓመት በተለያዩ ደማቅ ስነ ስርዓቶች ተቀብለዋል።

You might also like
Comments
Loading...