Fana: At a Speed of Life!

የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያዊነትን ልዩ ልዩ ፀጋዎች እያሳየን፣ እያከበርንና እየጠበቅን የምናከብረው በዓል ነው – ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2011( ኤፍ ቢሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ 13ኛውን የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ ለሀገሪቱ ህዝቦች መልዕክትን አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ኢትዮጵያ መንትያና ምትክ የሌላት አንዲት ሀገር ብትሆንም፥ ኢትዮጵያውያነት ግን በብዙ ህብር የሚገለፅ የዚህች ሀገር ዜጎች ድምር ፀጋ መሆኑን ጠቁመዋል።

እነዚህ የአንድ አካል ልዩ ልዩ ክፍሎች የሆኑት መልኮቿና ህብሮቿ፣ ብሄርና ብሄረሰቦቿ ናቸው ብለዋል። ውህደቱ ጠንካራ አንድነትን ይፈጥራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አንድነት ሲባል ግን አንድ ዓይነትነት እንዳልሆነ ግን ሁሌም መረዳት ይግባል ነው ያሉት።

አንዳንዶች አንደ ህዝብ እየገጠሙ ላሉ ችግሮች መፍትሄው “አንድ ዓይነትነት” እንደሆነ ያስባሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ሆኖም አንድ ዓይነትነት ለችግሮቻችን ጊዜያዊም ሆነ ዘላቂ መፍትሄ  ወይም ለጥንካሬያችን ዋስትና አለመሆኑን ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ ከጎረቤት ሀገር ታሪክ ልንማር እንችላለን ብለዋል።

በአጠቃላይ ብዝሃነት ፀጋ እንጂ እርግማን አለመሆኑን መረዳት እንደሚገባ ገልፀዋል።

አዳዲስ ጋሬጣዎችን ለማለፍ የህዝብ ብዝሃነት እንደሚያስፈልግ እና ሀሳብን አዋህዶ በጠንካራ የሀሳብ ድልድይ በመሻገር ጋሬጣዎቻችንን ለማለፍ የምናደርገው ጥረት ሀገር የመሆናችንን ትርጉም እንደሚያጎላው አንስተዋል።

እውቀት ወደ አንድነት ሲመራ ድንቁርና ግን መለያየትን ያመጣል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በትናንሽ ሀሳቦች ስንመራ የበለጠ እንኮስሳለን እንጂ የምናተርፈው ምንም ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በረዥም የትሰስር ዘመናቸው ቅጥር ሰርተው ተክለው አለመቀመጣቸውን በማንሳትም፥ ሲጋቡ፣ ሲዋለዱ፣ ሲዛመዱ፣ ሲወራረሱ እና አንዱ ወደ ሌላው በግልም በውልም ሲሄዱ የቆዩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከዘመናት በፊት እንዴት አብረን ስንኖር እንደነበር፣ እንዴት ስንወራረስ እንደኖርን ተረቶቻችን ታላቅ ምስክሮች ናቸው ብለዋል በመልዕክታቸው።

አዳዲሶቹ የጥላቻ ትርክቶች ከመምጣታቸው በፊት አብረው የኖሩት ተረቶቻችን ምን ያህል እንደ ስፌት የተሳሰርን፣ እንደጥለት ያማርን፣ እንደቤተሰብ አብረን የኖርን፣ እንደ ማህበረሰብ የተዛመድንና የተጋመድን መሆናችንን ይመሰክራሉ ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ኑሮና ህይወት እጣ ፈንታ በቋንቋ ልዩነት ያልቀተነበበ፣ በሚጋሯቸው መልክዓ ምድሮች እና የተፈጥሮ ፀጋዎች ሁሉ በጋራ በገነቧቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተቋማት አንድ የሆኑ የኢትዮጵያ ልጆች መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመግለጫቸው ላይ ጠቅስዋል።

ብዘሃነታችን ሳይነጣጥለንና ሳይከፋፍለን አንድነታችንም ሳይጠቀልለንና ሳይውጠን በዝተንና ሞልተን ኖረናል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊነት እንደ ኩሬ ውሃ ፀጥ ብሎ የተኛ ሳይሆንም በብሄሮችና ብሄረሰቦች መስተጋብር  ምክንያት እንደ ባህር የሚታደስ፣ እያደገ እየዳበረና እየጠነከረ የሚሄድ የህዝቦች እሴትና ህልም መሆኑን አስረድተዋል።

እኛ አንድም ብዙም ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከእኛ ባህልና ቋንቋ ውጪ የሆኑ ወገኖችን የምንቀበልባቸው፣ ተገፍቶ ለመጣ  ሰው ጥብቅና የምንቆምባቸው፣ አብሮን ለመኖር ለመጣ ሰው ከብሄረሰቡ የበለጠ መብት የምንሰጥባቸው ባህሎቻችን እና ወጎቻችን የዚህ መገለጫዎቻችን ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጋራ የመሰረትናት፣ ያቆየናት፣ የሞትንላት እና እዚህ ያደረስናት ሀገራችን ናት በማለትም የአንዱ ታሪክ የሌላው፤ የአንዱ መከራም የሌላው አንዱን መንካት ሌላውን መንካት የሆነባት ሀገር መሆኗን በመግለጫቸው አንስተዋል።

ከዚህ ታሪክ፣ ባህል እና ልምድ ውጪ ጠላትነትን፣ ጥላቻን፣ መገፋፋትን እና መራራቅን የሚዘሩብንን ኩሩው ባህላችን አይታገሳቸውም ብለዋል። የዘሩትን እንነቅልባቸዋለን እንጂ እንዲያበቅሉት አንፈቅድላቸውም ሲሉ አረጋግጠዋል።

ልዩነቶቻችንን አጉልተው እንደ ገደል ያራራቀን ለሚያስመስሉት የአንድነት ታሪካችንንና ባህላችንን ከፍ አድርገን እናሳያቸዋለን ሲሉም ገልፀዋል።

የሚለያዩን ሲመስሉን ይበልጥ እንደመራለን፣ የተቃረንን ሲመስላቸው ይበልጥ እንደ ድርና ማግ ተሳስረን አንድ ሸማ እንሆናለን ብለዋል።

አዲሱን የለውጥ ጎዳና በመደመር መንፈስ ጀምረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህን ተስፋ ሰጪ ለውጥ የሰላም መደፍረስ፣ የብሄር ግጭት፣ የጅምላ ፍርድና ስሜታዊነት ለአደጋ እንዳያጋልጡት ልንጠብቀው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ይህ በዓል ለይስሙላ የምናከብረው ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የምናደርግበት ትርጉም ያለው በዓል ነው በማለት፥ ሁሉም “ሆ” ብሎ በመውጣት የኢትዮጵያዊነትን ልዩ ልዩ ፀጋዎች እያሳየን፣ እያከበርንና እየጠበቅን የምናከብረው የህብራዊ አንድነታችን መገለጫ በዓል ነው ብለዋል።

ልዩነታችን የአንድነታችን ፀጋ፣ አንድነታችንም የልዩነታችን ተደማሪ ዋጋ መሆኑን የምንገልጥበትም ታላቅ በዓል ነው በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

 

You might also like
Comments
Loading...