Fana: At a Speed of Life!

ከህመም ስሜት ለማገገም የሚረዱ ቀለል ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአካል ብቃት እንቅስቃሴን መስራት በርከት ያሉ የጤና ጠቀሜታዎች እንደሚያስገኝልን በተለያዩ ጊዜያት የተሰሩ ጥናቶች ያመለክታሉ።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ከሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች ውስጥ የህመም ስሜቶችን ማስታገስ አንዱ ሲሆን፥ እኛም የህመም ስሜቶችን ለማስታገስ የሚረዱ ቀለል ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አይነቶችን እንጠቆምዎ፦

የእግር ጉዞ

ለበርካቶች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስሎ የማይታየው የእግር ጉዞ ከበሽታ ስሜት በቀላሉ ለማገገም ከሚመከሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ውስጥ አንዱ ነው።

የእግር ጉዞ ካሎሪን በማቃጠል ጤናማ የሰውነት ክብደት እንዲኖረን ከማድረግ ጀምሮ የልብ ጤንነትን እስከ መጠበቅ ድረስ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት።

በየቀኑ ቢያንስ ለ10 ደቂቃ የእግር ጉዞ ማድረግ የሚያስገኘው የጤና ጠቀሜታ በርካታ መሆኑ ነው የሚነገረው።

የውሃ ዋና

የውሃ ዋናም ጤንነትን ለመጠበቅ ከሚረዱ የአካል ብቃት እንቅሰቃሴዎች የሚጠቀስ ሲሆን፥ በተለይም የጀርባ ወይም የመገጣጠሚያ ህመምን ለማስታገስ ጠቀሜታው ከፍ ያለ መሆኑ ነው የሚነገረው።

ውሃ ውስጥ በቀላሉ ከአንድ አቅጣጫ ወደ ሌላ አቅጣጫ ብቻ መዋኘት የህመም ስሜቶችን ለማስታገስ በቂ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ታኢ ቻይ

ታኢ ቻይ በ13ኛው ክፍለ ዘመን በቻይና የተጀመረው የካራቴ ስፖርት አይነት ሆኖ በጣም በዝግታ የሚሰራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሆኑ ነው የሚነገረው።

ታኢ ቻይ በጣም በዝግታ፣ ትንፋሽ በመሰብሰብ እና በተመስጥኦ ውስጥ በመሆን ፍሰት ባለው መልኩ የሚሰራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሆኑም ተገልጿል።

የታኢ ቻይ የአካል ብቃት እንቅሰቃሴ በታችኛው የጀርባ ክፍል የሚከሰት ህመም እና የጡንቻ ህመምን ለማስታገስ የሚረዳ ሲሆን፥ እንደ ጭንቀት ካሉ ስሜቶችም በቀላሉ ለመፋታት ያግዛል ነው የሚባለው።

ከዚህ በተጨማሪም የታኢ ቻይ የአካል ብቃት እንቅሰቃሴ የላይኛውን እና የታችኛውን የሰውነት ክፍል ጡንቻ ለማጠንከር እንደሚረዳም ተነግሯል።

ዮጋ

በህንድ መነሻውን ያደረገው የዮጋ ስፖርት በብዛት ሰውነትን ለማፍታታና  ለማጠንከር የሚረዳ ሲሆን፥ አተነፋፈስ ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሰራ መሆኑም ይነገራል።

የዮጋ ስፖርት ለመላው አካላችን እና ለአእምሯችን ጤንነት ጠቀሜታ አለው የተባለ ሲሆን፥ ይህም ሰውነታችን ጠንካራ እንዲሆን እና አእምሯችንም አዎንታዊ ነገሮችን አንዲያስብ የሚያስችል ነው።

በማንኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚሰራው የዮጋ ስፖርት በተለይም የጀርባ ህመምን በሳስታገሱ በኩል ፍቱን መሆኑም ይነገርለታል።

በተለይም የጀርባ አጥንታችንን (ህብለ-ሰረሰራችንን) ለማፍታታት፣ ጡንቻንንና ነርቮችን ለማፍታታት፣ አጥንቶቻችን እርጥበትና ጥንካሬ እንዲያገኙ ለማድረግ እና በሰውነታችን ውስጥ ጥሩ የሆነ የኦክስጅንና የደም ዝውውር እንዲኖር እንደሚያደርግም ተገልጿል።

ምንጭ፦ huffingtonpost.co.uk

You might also like
Comments
Loading...