Fana: At a Speed of Life!

“እኔ አልሞትኩም፤ በቦታዬም አምሳዬ የሆነ ሰው ስልጣኑን አልተቆናጠጠም” – ፕሬዚዳንት ቡሃሪ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪ “ሞተዋል እሳቸውን የሚመስል ሰውም በቦታቸው ተተክቶቷል” የሚለውን ዜና ሐሰት መሆኑንና ራሳቸው መሆናቸውንም አስታወቁ፡፡

ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ትናንት እንዳስታወቁት “እኔ ትክክለኛው ቡሃሪ ነኝ ይህንንም አስረግጬ እነግራችኋለው” ብለዋል፡፡

ቡሃሪ ፖላንድ በሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ በዚያ የሚገኙ ሲሆን፥ ምላሹንም የሰጡት በዚያ ከሚኖሩ ዜጎቻቸው ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡

ይህንንም ዜና የሚያሰራጩ አካላት ኃላፊነት የጎደላቸውና ህግ አልባ ግለሰቦች ናቸው ብለዋል፡፡

ሰሞኑን ከሱዳን መጣ የሚባል የቡሃሪን አምሳያ የያዘ ሰው በትረስልጣኑ ላይ መቀመጡን ሲናፈስ መቆየቱ ተነግሯል፡፡

በርግጥ ቢቢሲ ኤኤፍፒን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ነገሩ የሰሞኑ ብቻ ሳይሆን ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ በአምሳያቸው ስለመተካታቸው እየተነገረ እንደነበር አንስቷል፡፡

መረጃው በማህበራዊ ሚዲያ  ከ500 ሺህ ጊዜ በላይ የታየ ሲሆን፥ ነገሩን በማሰራጨት ውስጥ ቀደም ብለው ፕሬዚዳንት የነበሩት ጉድ ላክ ጆናታንን ጨምሮ የቢያፍራው ተገንጣይ ቡድን መሪ እንደሚገኙበትም ተገልጿል፡፡

ቡሃሪ በቅርቡ በናይጄሪያ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሀገሪቱን ለሁለተኛ ጊዜ ለማስተዳደር እንደሚወዳደሩ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

ምንጭ፦ቢቢሲ

በአብርሃም ፈቀደ

You might also like
Comments
Loading...