Fana: At a Speed of Life!

“አባ ቶርቤ” በሚል መጠሪያ በድብቅ ሰዎችን በመግደልና በማስገደል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ቁጥር 15 ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “አባ ቶርቤ” በሚል መጠሪያ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በድብቅ በመንቀሳቀስ ሰዎችን ሲገድሉና ሲያስገድሉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው።

የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እንዳስታወቀው፥ ብሄራዊ የመረጃ እና የደህንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል በፀጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ያሉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር 15 ደርሷል።

ተጠርጣሪዎቹ “አባ ቶርቤ” (ባለሳምንት) በሚል መጠሪያ በመደራጀት ሰላማዊ ዜጎችን፣ የመንግስት ባለስልጣናት እና የፀጥታ ሀይሎችን ሲገድሉ እና ሲያስገድሉ ነበር በሚል ነው ተጠርረው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ከተጠርጣሪዎች መካከል ጋዲሳ ነጋሳ ጫላ፣ መርጋ ተፈራ ቡልቹ እና አኒሳ ጌታቸው የተባሉ የሚገኙበት ሲሆን፥ በደምቢዶሎ፣ ነቀምትና ሰሜን ሸዋ በንፁሃን ዜጎች ላይ ሲፈፀም የነበረዉን ግድያ ሲያቀነባብሩ የነበሩ ናቸው ተብላል።

ተጠርጣሪዎቹ ከተለያዩ ሽጉጦች፣ ቦምቦች እና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መረጃ እንደሚያመለክት ነው ቢሮው ያስታወቀው።

ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፥ በመዲናዋ የከተሙትም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን እና አክቲቪስቶችን ለመግደል እንደሆነም ተደርሶበታል።

ዛሬ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሀይሎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እነደነበራቸዉም ተሰምቷል።

የተቀሩትን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያስታወቀው የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፥ የተጠርጣሪዎቹን ተግባርና ማንነት በተመለከተ በቅርቡ ዝርዝር መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

 

 

You might also like
Comments
Loading...