Fana: At a Speed of Life!

በ 2018 ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዞች መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ህዳር 27፣2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአሁኑ ወቅት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዞች መጠን ከምን ጊዜውም  በላይ እየጨመረ መሆኑ ተገለፀ።

ለዚህ ምክንያቱም  የመኪና ተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመር ተከትሎ በዓለም  ላይ ያለው የመኪናዎች ገበያ በሚገርም ፍጥነት እያደገ መሄዱ  ነው ተብሏል።

እነዚህ መኪናዎች ከሚጠቀሙት ነዳጅ ዘይት የሚወጣው የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ጭስም በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ደረጃ መደረሱ ነው የተገለፀው።

ይህ ሁኔታም በአለም ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ሀገሮች ላይ በይበልጥ እንደሚስተዋል መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በቅርቡ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው በካይ ጋዝ መጠን 2 ነጥብ 7 በመቶ መጨመር ዋነኛ ምክንያት ቻይና፥  በያዝነው ዓመት የድንጋይ ከሰልን እንደ አማራጭ የሃይል ምንጭ መጠቀሟ ነው ተብሏል።

በሌላ በኩል በዓለም ላይ ከመኪናዎች ፣ከአውሮፕላኖች እና ከፋብሪካዎች የሚወጡ መርዛማ ጋዞች ከባቢ አየሩን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መበከላቸው ተጠቁሟል።

እንደ አለም አቀፉ የካርበን ልቀት ተቆጣጣሪ ድርጅት ጥናት በያዝነው ዓመት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዞች መጠን በ2 ነጥብ 7 በመቶ ጨምሯል።

በጥናቱ  ከባለፈው ዓመት ከነበረው የልቀት መጠን ላይ በ 1 ነጥብ 6 በመቶ በላይ ጭማሬ ማሣየቱ ነው የተገለፀው።

ለዚህም በዓለም ከፍተኛውን በካይ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር የምትለቀው ቻይና በቀዳሚነት የምትጠቀስ ስትሆን፥  አሜሪካ ደግሞ በሁለተኛ  ደረጃ ላይ ትገኛለች ።

የአውሮፓ ሀገሮች በካይ ጋዝን ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ ሶስተኛውን ደረጃ የሚይዙ ሲሆን ፥ በቅደም ተከተል ህንድ፣ ሩሲያ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ኢራን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ደቡብ ኮሪያና ካናዳ ደግሞ ተከታዩን ደረጃ ይይዛሉ ተብሏል።

እነዚህ ሀገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን የበካይ ጋዝ መጠን የማይቀንሱ ከሆነ በ2020 ላይ የአለም የሙቀት መጠን አሳሳቢ ደራጃ ላይ የሚደርስ መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል።

ስለሆነም ሀገራቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 ፓሪስ ላይ የተፈራረሙትን ስምምነት ማክበር ተቀዳሚ ተግብር ሊሆን ይገባል ነው የተባለው።

በመጨረሻም ጥናቱ  እነዚህ ሀገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን የካርቦንዳይ ኦክሳይድ መጠን እንዲቀንሱና በምትኩም ታዳሽ የሃይል ምንጭን በመጠቀም በዓለም ላይ እየተከሰተ ያለውን  የአየር ንብረት ለውጥ እንዲታደጉ ጥሪ ቀርቧል።።

 

ምንጭ ፦ቢቢሲ

 

 

You might also like
Comments
Loading...