Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የምክክር መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
 
የምክክር መድረኩ “በአንድነት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር” በሚል መሪ ቃል ነው በዛሬው እለት የተካሄደው።
 
በአዲስ አበባ የኦሮሞ ባህል ማእከል አዳራሽ በተካሄደው የምክክር መድረኩ ላይም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 14 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል።
 
በውይይት መድረኩ ላይም የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ምክትል ሊቀ መንበርና የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ተገኝተዋል።
 
የኦዲፒ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በመድረኩ ላይ የመነሻ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን፥ በዚህም የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከየት ወደየት በሚለው እና አሁን ባለበት ደረጃ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 
የኦዲፒ ምክትል ሊቀ መንበርና የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተባበረ መንፈስ በጋራ መስራት እንዳለባቸው አንስተዋል።
 
“ጠላት በየእለቱ በሚሰጠን አጀንዳ ላይ እየተባላን ውለን እንድናድር እያደረገ ነው” ያሉት አቶ ለማ መገርሳ፥ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ አንዱን በመረዳት እና በዘመናዊ የፖለቲካ መስመር በሽግግር ወቅት ላይ እያገጠመ ያለውን አለመረጋጋት ማለፍ እንዳለባቸውም አስታውቀዋል።
 
ጠላት ከውጭ ሆኖ እሳት እየወረወረብን ኦሮሚያን የብጥብጥ አውድማ ለማድረግ ቀን ከሌት እየሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ የኦሮሚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለችግሩ መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ ችግሩን የሚያባብሱ ተግባራትን ሲፈፅሙ እንደሚስተዋልም ነው አቶ ለማ የተናገሩት።
 
በዚህ መንገድ የሚመጣ ጉዳት የሁላችንም በመሆኑ ችግሩን አንድ ወገን ላይ ጥሎ ከመመልከት ይልቅ በተጠናከረ አንድነት ማለፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መስማማት ያስፈልጋል ብለዋል።
 
የኦዲፒ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በመድረኩ ላይ የመነሻ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን፥ በዚህም የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከየት ወደየት በሚለው እና አሁን ባለበት ደረጃ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 
እንዲሁም የኦሮሞ ህዝብ ቀጣይ የትግል ምእራፍ አቅጣጫ ዙሪያም በመነሻ ሀሳባቸው ዘርዝረዋል።
 
የምክክር መድረኩ ዓላማም በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኦሮሞ ህዝብ ዙሪ በጋራ መስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ተብሏል።
 
በሙለታ መንገሻ
You might also like
Comments
Loading...