Fana: At a Speed of Life!

በሞሱል በደረሰ የጎርፍ አደጋ ነዋሪዎች መኖሪያቸውን ለቀው ወጡ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሞሱል በደረሰ የጎርፍ አደጋ ነዋሪዎች መኖሪያቸውን ለቀው ወጡ።

በኢራቅ ሰሜን ሞሱል ባለፉት 2 ቀናት የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት ከተለያዩ የሰሜን ሞሱል አካባቢዎች 85 ያህል አባዎራዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው ተገልጿል።

የጎርፍ አደጋው የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ ከማስተጓጎሉም በሻገር ትምህርት ቤቶችና ሌሎች አገልግለሎት መስጫ ተቋማት እንዲዘጉ አድርጓል ተብሏል።

በአካባቢው ስድስት ድልድዮችና ኒምሩድ በተባለው የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ 300 የመጠለያ ድንኳኖችንም ማፍረሱ ተነግሯል።

በሰሜን ሞሱል በሰሞኑ የጎርፍ አደጋና ከፈረንጆቹ 2014 እስከ 2017 በኢራቅ መንግስት እና አይ ኤስ አይ ኤስ ተዋጊዎች መካከል በተካሄደው ጦርነት መሰረተ ልማቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን የሀገሪቱ መንግስት ትልቅ የቤት ስራ እንዳለበት ነው የተገለጸው።

የአካባቢውና የኢራቅ ማዕከላዊ መንግስት የውጭ ባለሙያዎችን በማሳተፍ የከተማዋን የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ማሻሻል እንደነበረበት ነዋሪዎቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የጎርፍ አደጋው ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህ ሳምንት መጨረሻም በአብዛኛው የኢራቅ አካበቢዎች ከፍተኛ ዝናብ እንደሚጠበቅ ነው የተገለጸው።

ምንጭ፦ አልጀዚራ

You might also like
Comments
Loading...