Fana: At a Speed of Life!

ለብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል አከባባር ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 26 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ13ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል አከባባር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።

ቅዳሜ እስከሚካሄደው ዋናው በዓል ድረስ የሚካሄዱ መርሃ ግብሮቹንም አስተዳደሩ ይፋ አድርጓል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ሃላፊ ወይዘሪት ፌቨን ተሾመ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ከ2 ሺህ የሚበልጡ የብሄር ብሄረሰብ ተወካዮች ወደ ከተማዋ እየገቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በነገው እለትም የበዓሉ አካል የሆነና በመስቀል አደባባይ የሚከናወን የቡና መጠጣት ስነ ስርአት ይኖራል ብለዋል።

የቡና መጠጣት ስነ ስርዓቱ በአይነቱ ለየት ያለ እና ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች የሚታደሙበት እንደሆነም ተገልጿል።

“ኑ ለሰላም ቡና እንጠጣ” በሚል መሪ  ሃሳብ የሚካሄደውን ይህን የቡና መጠጣት ስነ ስርዓት በአለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም “ህብር ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በጊዮን ሆቴል የሚካሄድና የበዓሉ አካል የሆነ የሙዚቃ ድግስም ይኖራል ነው ያሉት።

በሙዚቃ ድግሱ አንጋፋና አዳዲስ ድምጻውያን ለከተማው ነዋሪና ለብሄር ብሄረሰብ ተወካዮች ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ።

ታዳሚዎቹ የብሄር ብሄረሰብ አልባሳትን በመልበስ በሙዚቃ ድግሱ በነጻ መታደም እንደሚችሉም ተገልጿል።

ዋናው በአል ህዳር 29 ቀን ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታዲየም፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ከ30 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች እና የብሄር ብሄረሰብ ተወካዮች በተገኙበት በደማቅ ስነ ስርዓት ይከበራል።

የዘንድሮው በዓል አንድነትን እና ሰላምን ማጠናከር ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚከበር መሆኑ ተጠቅሷል።

በእለቱ ጥቅም ላይ የሚውሉ ህትመቶች ከወዲሁ የተጠናቀቁ ሲሆን፥ ከዚህ ጋር በተያያዘም ሴቶች እና ወጣቶች እንዲሳተፉ እድል የተፈጠረበት እና ከስራ እድል እስከ ገበያ ትስስር መፍጠር የተቻለበት መሆኑም ተነስቷል።

በዓሉን በሰላም ለማጠናቀቅም የጸጥታ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም ሃላፊዋ ጠቅሰዋል።

 

 

በሃብታሙ ተክለስላሴ

 

 

 

 

 

You might also like
Comments
Loading...