Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉ የሜቴክ ሰራተኞች ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን ጊዜ ፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሙስና የተጠረጠሩ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሰራተኞች በትናንትናው ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ሰሞኑን በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች የቀረቡት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ነው።

በሙስና ወንጀል እነ ብርጋዴየር ጀኔራል ጠና ቁርዲ፣ ብርጋዴር ጄነራል በረኸ በየነ፣ ብርጋዴር ጄነራል ጥጋቡ ፈትለአብ እና ብርጋዴር ጄነራል ሀድጉ ገብረጊዮርጊስን ጨምሮ 28 ተጠርጣሪዎች ናቸው ፍርድ ቤት የቀረቡት።

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ ሀላፊነት ስፍራ ሲሰሩ የግዢ መመሪያን ባለመከተል እና 3ኛ ወገን እና ራሳቸውን ለመጥቀም በማሰብ ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት 28 ዓመት ያገለገሉና ጥቅም የማይሰጡ ናቸው የተባሉ መርከቦችን በመግዛት፤ መርከቦቹ ዱባይ እና ጂቡቲ እንዲጠገኑ 29 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ማውጣታቸውን አስታውቋል።

ጥገናውን ካከናወኑ ድርጅቶች እስከ 10 በመቶ ኮሚሽን በመቀበል ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ውጭ ሀገራት ማሸሻቸውን እና ለግል ጥቅም ማዋላቸውን ፖሊስ ገልጿል።

በተጨማሪም ሁለት መርከቦችን በህገ ወጥ ንግድ ማሳተፋቸውን ጠቅሷል።

ከዚህ ባለፈም ለያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ የመሳሪያ ግዢ ሳይፈጸም ክፍያ እንዲፈጸም አድርገዋል ያለው ፖሊስ፥ እንዲሁም በፋብሪካው አፈር እንዲሸሽ 30 በመቶ የሲቪል ስራው በባለሙያ እንዲጠና መድረግ ሲገባው፤ ሳይጠና 3ኛ ወገንን ለመጥቀም በማሰብ ከፍተኛ ክፍያ በመፈፀም አፈሩ የሸሸ ሆኖ እንዲቀርብ ተደርጓል ብሏል ፖሊስ።

በተጨማሪም በማይመለከታቸው የሆቴል ግዢ ላይ በመሰማራት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ወጪ ማድረጋቸውንም ነው ፖሊስ ያስታወቀው።

ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የምንጣሮ ስራ በአግባቡ ሳይሰራ ለተለያዩ ድርጅቶች ገንዘብ ተከፍሏል ያለው ፖሊስ፥ የተወሰኑት ድርጅቶች ገንዘብ ተቀብለው ምንጣሮ ሳያከናውኑ መጥፋታቸውንም አስረድቷል።

ተጠርጣሪዎቹ ቁርጥራጭ ብረቶችን ከተለያዩ የልማት ድርጅቶች ተረክበው በመሸጥና ለግል ጥቅማቸው በማዋል እንዲሁም ከስኳርና ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ በ21 መዝገቦች የተደራጀ መረጃ ቀርቦባቸዋል።

መርማሪ ፖሊስ ውልና ክፍያ የተፈፀመባቸውን ሰነዶችን መሰብሰቡን እና ከ20 በላይ መቀበሉን በመጥቀስ፤ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው ከፍርድ ቤት መያዣ ውጭ መያዛቸውን እና በ48 ሰዓት ውስጥ ፍረድ ቤት አለመቅረባቸውን በማስረዳት፤ በዋስ ወጥተው ውጭ ሆነው ጉዳያቸውን ለመከታተል ጠይቀዋል።

12ኛ ተጠርጣሪ ኮሎኔል አዜብ ታደሰ በበኩላቸው፥ “በወታደር ቤት አመንኩበትም አላመንኩበትም ትዕዛዝ አልቀበልም አይባልም” ብለዋል።

የመርከቦቹ ሽያጭ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ሲያገለግሉ ከአለቆች በተሰጠ ትእዛዝ መሰረት ያለግልጽ ጨረታ 12 ድርጅቶችን በኢንተርኔት ቀጥታ በማወዳደር ከፍተኛ ገንዘብ ላቀረቡ 8 ድርጅቶች መርከቡን ሸጠናል፤ ይህም የአለቆቻችንን ትዕዛዝ ለመፈፀም ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ፖሊስም ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር ያዋልኩት በፍርድ ቤት ትዕዛዝና በህጋዊ መንገድ ነው ያለ ሲሆን፥ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ቅዳሜና እሁድ በመሆኑ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍረድ ቤት ማቅረብ አለመቻሉን አስታውቋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤትም የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን ጊዜ የፈቀደ ሲሆን፥ ለህዳር 14 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like
Comments
Loading...