Fana: At a Speed of Life!

ጠጥቶ አውሮፕላን ሊያበር የነበረው ፓይለት ተያዘ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2011 (ኤፍቢሲ) ከተገቢው በላይ ጠጥቶ ሊያበር የነበረው ጃፓናዊው ፓይለት ሄትሮ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ መያዙ ተነገረ።

የ42 ዓመቱ ጃፓናዊ መጠጣቱ የተረጋገጠው ለማብረር ሰዓታት በሚቀሩበት ወቅት በተደረገበት የትንፋሽ ምርመራ ነው ተብሏል።

ቢቢሲ የጃፓን መገናኛ ብዙሃን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ፖሊስ በአካባቢው የአልኮል ሽታ በማሽተቱ ምክንያት ባደረበት ጥርጣሬ ነው ሊመረመር የበቃው ተብሏል።

ጃፓናዊው ፓይለት መጠጣት ከሚፈቀደው ዘጠኝ እጥፍ በላይ አልኮል መጎጨቱንም በጥያቄው ወቅት ማመኑ ተገልጿል።

ለአብራሪዎች የተቀመጠው አነስተኛ መጠን 20 ሚሊ ግራም አልኮል ሲሆን፥ በጃፓናዊው 100 ሚሊ ሊትር ደም ውስጥ 189 ሚሊግራም አልኮል መገኘቱ ተረጋግጧል።

አብራሪው በወቅቱ ከብሪታንያ ተነስቶ ወደ ጃፓን ቶኪይ ለማቅናት 50 ደቂቃዎች ብቻ ነበር የቀሩት፤ በዚህም ከ69 ደቂቃዎች መዘገየት በኋላ ጉዞውን ለመጀመር መገደዱ ተገልጿል፡፡

የጃፓን አየር መንገድ ወደፊት ይህን የመሰሉ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ እርምጃ እንድሚወስድ አስታውቆ መንገደኞች በመስተጓጎላቸው ምክንያት ይቅርታ ጠይቋል።

ጃፓናዊው በአሁኑ ወቅት  እስር ቤት ሆኖ ፍርዱን በመጠባበቅ ላይ ሲሆን በዚያው በብሪታንያ ከአራት ወራት በፊት ተመሳሳይ ጥፋት ፈጽሞ የተገኘ አንድ አብራሪ የስምንት ወራት እስር ተፈርዶበት ዘብጥያ መውረዱ የሚታወሳ ነው።

 

 

 

ምንጭ፦ቢቢሲ

በአብርሃም ፈቀደ

You might also like
Comments
Loading...